የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ‹‹Quality of Leishmanisis Case Management in SNNPR›› በሚል ርዕስ ግማሽ ሚሊየን ብር የተመደበለት የዳሰሳ ጥናት ለማከናወን እየተዘጋጁ ሲሆን በጥናቱ ለሚሳተፉ መረጃ ሰብሳቢዎችና ሱፐርቫይዘሮች መጋቢት 01/2013 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ዮሐንስ እንደገለጹት የምርምር ማዕከሉ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ትኩረት በሚሹ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች ላይ ያተኮሩና በሽታዎቹን ከመከላከልና ከማከም አንፃር ዘረፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸውን የምርምር ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ ከሥልጠና አንፃርም በበሽታዎቹ መከላከልና ሕክምና አሰጣጥ ዙሪያ ለበርካታ ጤና ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን ማዕከሉ እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የመድኃኒት ቁጥጥር ሥራዎችን እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ትኩረት ከሚሹ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች መካከል ሌሽማንያ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጸጋዬ በክልሉ ጤና ቢሮና በማዕከሉ ትብብር የሚከናወነው የዳሰሳ ጥናት በአርባ ምንጭ፣ በኮንሶ ካራትና ጂንካ ሆስፒታሎች ውስጥ የሌሽማንያ በሽታ የሕክምና አሰጣጥ ጥራትን መፈተሽ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጥናቱ ውጤትም እንደ ክልል በሌሽማኒያ በሽታ ሕክምና አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅርፍ ጥራት ያለው ሕክምና አሰጣጥ እንዲኖር ከማደረግ አንፃር የጎላ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል፡፡ በጥናቱ መረጃ በመሰብሰብና በሱፐርቪዥን ላይ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች የሚሰጠው ሥልጠና ለሠልጣኞች የጥናቱን ዓላማና ግብ ማሳወቅ፣ መረጃ እንዴት እንደሚሰበስቡና የትኞቹ መረጃዎች አስፈላጊ እንደሆኑ ማሳየት ላይ ያተኮረ እንደሆነ አቶ ጸጋዬ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማሌ ማቴ በበኩላቸው ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች በአብዛኛው የደሃ ሀገር በሽታዎች ተብለው የሚታወቁ መሆናቸውን ተናግረው አሁን ላይ እንደ ሀገር 11 በሽታዎች ተለይተው እየተሠራባቸው ነው ብለዋል፡፡ በደቡብ ክልልም በሽታዎቹን ለመከላከልና ለማከም በትኩረትና በዕቅድ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ከዚህም አንፃር በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጡ 3 ስትራቴጂዎችን ማለትም የግልና የአካባቢ ንጽህናን ማስጠበቅ፣ መድኃኒቶችን በአግባቡ መስጠትና ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ጥራት ያለው ሕክምና መስጠት የሚሉትን በመከተል ለመሥራት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከስትራቴጂዎች አንፃር በተለይ በሌሽማኒያ በሽታ ሕክምና አሰጣጥ ጥራትና ውጤታማነት ዙሪያ እንደ ክልል ችግሮች እየታዩ በመሆናቸው፣ የሕክምና አሰጣጥ ጥራቱን ለማሻሻል ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ እንዲሁም ችግሮቹን ጥናት ላይ በመመሥረት ለመፍታት በማለም የክልሉ ጤና ቢሮ በመስኩ ምርምሮችን በመሥራት ከፍተኛ ልምድ ካለው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ጋር ጥናቱን ለማከናወን የትብብር ስምምነት ተፈራርሞ ወደ ሥራ መግባቱን አውስተዋል፡፡

በጥናቱም በህሙማን ክትትል፣ በላቦራቶሪ ምርመራ፣ በመድኃኒት አሰጣጥ ወዘተ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች በጥልቀት እንደሚፈተሹና በዚህም ላይ ተመሥርቶ የሕክምና አሰጣጥ ጥራቱን ለማሻሻል እንደሚሠራ አቶ ማሌ ጠቁመው ሥልጠናው ጥናቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ከማከናወንና የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከማስቻል አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 የተመሠረተው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል በ2025 በምሥራቅ አፍሪካ ትኩረት በሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምር፣ ሥልጠናና ማማከር የልኅቀት ማዕከል የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሠራ የሚገኝ የምርምር ማዕከል ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት