የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሰላም ፎረም አባላትና የ2014 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች ‹‹በፍቅር በመደመር ሰላማችንን እንጠብቅ›› እና ‹‹100 ቀናችንን በጽዳት ዘመቻና ችግኞችን ውሃ በማጠጣት እናሳልፍ›› በሚሉ መሪ ቃሎች በዋናው ግቢ የጽዳት ዘመቻና ችግኝ ውሃ የማጠጣት መርሃ-ግብር አካሂደዋል፡፡

የፎረሙ ፕሬዝደንት ተማሪ ጴጥሮስ ሀሮ ፎረሙ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማርና ሌሎች የአስተዳዳር ዘርፍ ሥራዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወኑ ለማገዝ የተቋቋመ መሆኑን ተናግሯል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሰላም ረገድ እንደ ተምሳሌት የሚጠቀስ ነው ያለው ተማሪ ጴጥሮስ ይህንን ለማስቀጠል መርሃ-ግብሩ ከግቢ ጽዳቱ ጎን ለጎን ስለ ሰላም በመነጋገር የግንዛቤ ማሳደግ ዘመቻ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ዘመቻው በቀጣይ በሌሎች ካምፓሶች እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የፎረሙ ም/ፕሬዝደንት ተማሪ ቤተልሔም ዘመኑ የፎረሙ ዋነኛ ዓላማ ሰላምን ማስከበር በመሆኑ በተቋሙ ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ነገርችን ቀድሞ በማጣራት ችግሮቹ በውይይት እንዲፈቱ የሚያደርግ መሆኑን ገልጻለች፡፡

5ኛ ዓመት የሜካኒካል ምኅንድስና ተማሪና የሰላም ፎረም ፍርድ ሸንጎ ሰብሳቢ ተማሪ ኦብሳ ሳዲቅ ሸንጎው ወደ ሰላም ፎረም የሚመጡ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሚሠራ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በጋሞ ዞን ውስጥ እንደመገኘቱ የጋሞ አባቶችን ጥል የማብረድ ፈለግ በመከተል የማስታረቅ ሥራዎችን እንሠራለን ብሏል፡፡

የ5ኛ ዓመት የሰርቬይንግ ምኅንድስና ተማሪና የ2014 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች ተወካይ ተማሪ ማስተዋል ኃ/ኢየሱስ በዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ‹‹የ100 ቀን›› ፕሮግራምን ሲያከብሩ የውሃ መራጨት ቀን፣ የእብደት ቀንና ሌሎችም ስያሜዎችን በመስጠት ያልተገቡ ድርጊቶችን በመፈፀም ለግጭት ሲዳረጉ እንደነበር አስታውሷል፡፡ ይህን ልማድ ለማስቀረትና ለቀጣይ ተማሪዎችም መልካም አርአያ ለመሆን ከሰላም ፎረም ጋር በመተባበር በጽዳትና ችግኞችን ውሃ በማጠጣት ለማሳለፍ መወሰናቸውን ተማሪ ማስተዋል ተናግሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ የሰላም ፎረም አመራሮች፣ የ2014 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች እና ሌሎችም በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት