የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ለጊዶሌ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች የምልክት ቋንቋ ምንነት፣ የአካቶ ትምህርት ጽንሰ ሃሳብና አተገባበር፣ መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸው ጭብጦች ዙሪያ ከመጋቢት 14-15/2014 ዓ/ም በልዩ ፍላጎትና አካቶ ት/ክፍል መምህራን ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

በሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት የማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ዘበነ ተምትሜ መስማት የተሳናቸውና የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በት/ቤት ውስጥ ባላቸው ቆይታ መልካም መስተጋብርና ሳይቸገሩ መግባባት የሚችሉበት ሂደት እንዲፈጠር ታስቦ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት የልዩ ፍላጎትና አካቶ ት/ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ ውድነሽ አስጨናቂ እንደተናገሩት የአካቶ ትምህርት ጽንሰ ሃሳብና አስፈላጊነት እንዲሁም በት/ቤቱ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች እንደየባህሪያቸው መለየት ላይ በሥልጠናው ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም የአካቶ ትምህርት ትግበራ ማነቆ የሆኑ ችግሮች ዙሪያ የጋራ ውይይት የተደረገ ሲሆን በልየታ የቀረቡ ችግሮችን ለመፍታት ከመንግሥት፣ ከመምህራን፣ ከተማሪዎች እንዲሁም ከኅብረተሰቡ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ያሉ በመሆኑ ት/ቤቱ የድርሻውን እንዲወጣ ሥልጠናው ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የት/ክፍሉ መምህር አቶ ታደሰ እንግዳ በበኩላቸው የምልክት ቋንቋን ለመጠቀም የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን በማመላከት የሥልጠናው ሂደት በጽንሰ ሃሳብ፣ በቪዲዮ በማስደገፍና በተግባር የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዋናነት መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች በምን መልኩ መማር እንዳለባቸው ተተኳሪ በማድረግ የጣት ፊደላት ንባብ፣ የከንፈር ንባብ፣ በሰውነት እንቅስቃሴ መግባባት የሚቻልበትን መንገድ ማሳየታቸውን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በት/ቤቱ በዕለት ተዕለት ተግባራት ዘወትር ሊጠቀሙባቸው የሚችሉባቸው ቃላት ዙሪያ በማተኮር ሥልጠናው መሰጠቱን የገለጹት አቶ ታደሰ በት/ቤቱ በዘርፉ የሠለጠኑ መምህራን መገኘታቸው በሥልጠናው ክሂሎታቸውን አዳብረው በአካቶ ትምህርት ትግበራ ላይ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት አገልግሎቱ ከሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት ጥሩ መነሻ ማግኘታቸውንና በተለያየ መንገድ ራሳቸውን ለማሳደግና ድጋፍ ለመስጠት ጥሩ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው 35 መምህራን፣ 7 የአስተዳደር ሠራተኞችና 7 መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡