የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ፊዚክስ ት/ክፍል ከጋሞ ዞን ወረዳዎች ለተወጣጡ 29 የፊዚክስ መምህራን በኅዋ ሳይንስ ምርምር ዙሪያ እንዲሁም ለት/ክፍሉ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች የምርምር ጽሑፍ አዘገጃጀትን አስመልክቶ ከመጋቢት 14-17/2014 ዓ/ም የቆየ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ እንደገለጹት በኅዋ ሳይንስ ዘርፍ ወጣቶችን ለማነቃቃት በጋሞ ዞን ባሉ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ላይ መሠራት እንዳለበት በመታመኑ የፊዚክስ መምህራንን የኅዋ ሳይንስ ግንዛቤ ለማሳደግ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ ሥልጠናው መምህራን በየትምህርት ቤታቸው ክበባትን አዋቅረው ለተማሪዎቻቸው ስለ ኅዋ ሳይንስ ምርምር ግንዛቤን እንዲፈጥሩ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ የማኅበረሰብ አገልገሎት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም በበኩላቸው ሥልጠናውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስትሮኖሚና አስትሮ ፊዚክስ ዲፓርትመንት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ማሪያና ፖቪክ /Dr. Mirjana Povic/ በበጎ ፈቃደኝነት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኅዋ ሳይንስ ሙከራ ቁሳቁሶች ውድና በቀላሉ የማይገኙ መሆናቸውን የተናገሩት አስተባባሪው ሥልጠናው መምህራን በአካባቢያቸው በቀላሉ የሚገኙና አገልግሎት የማይሰጡ ቁሳቁሶችን ተጠቅመው ሥርዓተ ፀሐይ/Solar System/፣ የብርሃን ፍጥነት፣ የብርሃን ጨረርና የመሳሰሉ ጉዳዮችን ተማሪዎቻቸውን በቤተ-ሙከራ ማስተማር እንዲችሉ ግንዛቤ ያስጨበጠ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም አሠልጣኟ ለት/ክፍሉ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች የምርምር አጻጻፍ፣ ለኅትመት ማዘጋጀት፣ ጆርናሎችን መምረጥና ምርምርን ለኅትመት ማብቃትን በተመለከተ ሥልጠና መስጠታቸውን ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡