በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች አዘጋጅነት በኢንስቲትዩቶቹ የተለያዩ ሥራ ክፍሎች ለሚሠሩ ባለሙያዎች ከግንቦት 18-23/2014 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ 

የሁለቱ ኢንስቲትዩቶች ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ዘርይሁን በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ የቢሮ አስተዳደር ደንበኛ አያያዝና ኃላፊነት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የደብዳቤ አጻጻፍ፣ የሀብት አጠቃቀም እንዲሁም በ ‹‹MS Word›› እና ‹‹MS Excel›› የኮምፒውተር ሶፍትዌሮች አጠቃቀም ላይ ክሂሎት በማሻሻል የሠራተኞችን አቅም ማሳደግና ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን ንዋይ አብዛኛውን ጊዜ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ በአካዳሚክ ዘርፍ ብቻ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ተናግረው በተለያዩ የሥራ ክፍሎች የሚገኙ ባለሙያዎችን በማሠልጠን የግብዓትና የጊዜ ብክነትን ለመቅረፍ እንዲሁም የባለሙያዎቹን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተርና አሠልጣኝ አቶ ጌታሁን ትዕግስቱ እንደገለጹት ሥልጠናው ሀብትን ሊቆጥቡና ሥራዎችን በጋራ ሊያሠሩ በሚችሉ እንደ ‹‹Google Drive››፣ ‹‹Power Geez›› ‹‹Windows Defender›› የመሳሰሉ ፕላትፎርሞች ላይ ተሰጥቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የሰው ሀብት ንዑስ ሥራ ሂደት ቡድን መሪ ወ/ሮ ወደፊት ታደሰ በበኩላቸው ሠራተኞቹ ጊዜው በሚጠይቀው ልክ ከቴክኖሎጂዎች ጋር በመተዋወቅና ክሂሎታቸውን በማሳደግ ለደንበኞቻቸው ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች የሰው/ሀ/ን/ሥራ ሂደት፣ የፋይናንስና ግዢ፣ የሬጅስትራርና የጠቅላላ አገልግሎት ባለሙያዎች እንዲሁም የቢሮ አስተዳደሮችና ረዳቶች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት