የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የእንሰት ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም የማብላላት ሂደትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን በጋሞ ዞን ደጋማ አካባቢዎች በሚገኙ 4 ወረዳዎች ለሚኖሩ እንሰት አብቃይ አርሶ አደሮች ለማዳረስ 2.3 ሚሊየን ብር የተመደበለት ፕሮጀክት ቀርጾ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት እንሰት የመፋቅ፣ የመቁረጥ፣ የመጭመቅና የማብላላት ሂደትን የሚያዘምኑና የሚያሻሽሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ተገኝተው ለዓመታት በቤተ-ሙከራና በተግባር ተሞክረው ውጤታማ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በቴክኖሎጂዎቹ ተመራማሪውም ሆነ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ሽልማትና ዕውቅናዎችንም አግኝተዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ በስፋት ለማሻገር ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት የቀረበው ንድፈ ሃሳብ ተቀባይነት በማግኝቱ 2.3 ሚሊየን ብር ተመድቦ ቴክኖሎጂዎቹን በጋሞ ዞን በሚገኙ 4 ወረዳዎች ለማዳረስ ወደ ሥራ መገባቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ቴክኖሎጂዎቹን ለአርሶ አደሩ ከማዳረስ ባሻገር የእንሰት ምርትን ለማሳደግ በማለም የተመረጡ የእንሰት ዝርያ ችግኞችን በስፋት የማፍላት ሥራ የፕሮጀክቱ አካል ሆኖ እየተተገበረ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ ቴክኖሎጂዎቹን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ በአጠቃቀማቸው ዙሪያ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዶርዜ አካባቢ ለሚገኙ ሴት አርሶ አደሮች ከፕላስቲክ የተሠሩ ማብለያዎችና የማብላላት ሂደቱን የሚያፋጥን እርሾም ተሰራጭቷል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን በስፋት ማምረትና ማሰራጨት የፕሮጀክቱ ቀጣይ ትኩረት መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ተክሉ እንደ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን ደጋማ አካባቢዎች ካዳረስን በኋላ በቀጣይ በሌሎች ዞኖችና ክልሎች ለማዳረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንሠራለን ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንሰት ድርቅን የሚቋቋም፣ በትንሽ ቦታ ብዙ ምርት መስጠት የሚችልና በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን ሕዝብ በላይ በዋና ምግብነት የሚጠቀመው ተክል ቢሆንም በሀገር ደረጃ እንሰትን የሚመለከት ምንም ዓይነት የግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምም ሆነ ፖሊሲ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሰቲ፣ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ተቋማት አሁን ላይ ለእንሰት የሰጡት ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው ያሉት ዶ/ር አዲሱ መሰል ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ከሆነ መንግሥትም ሆነ ፖሊሲ አውጪዎች ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡ ዶ/ር አዲሱ እንሰት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ሰብል መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ጊዜያት ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚገጥመን የምግብ ቀውስ መፍትሔ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ያለው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪው ቴክኖሎጂዎቹን ሠርተን ከማቅረባችን በፊት ኅብረተሰቡን ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ዶርዜ ላይ ለዚሁ ሥራ ለተደራጁ ሴት አርሶ አደሮች የጤና መድኅን መገዛቱን የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ በ2015 በጀት ዓመት የመፋቂያ ማሽኖችንና የማብላላት ሂደቱን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛት አምርቶ ለተደራጁ አርሶ አደሮች ለማዳረስ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የዶርዜ ከተማ ነዋሪና እንሰት አምራች የሆኑት ወ/ሮ ብዙነሽ ዮቴ እና ወ/ሮ ብርቱካን ቴማ እንሰት በአካባቢያቸው የኑሮ መሠረት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንሰት ለምግብነት እስኪደርስ ያለው የሥራ ሂደት በእጅጉ አድካሚ ነው ያሉት አርሶ አደሮቹ በዩኒቨርሲቲው ተሠርተው የቀረቡት ማሽኖችና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ድካማቸውን የሚያስቀሩ በመሆኑ ከእጃቸው ደርሰው የሚጠቀሙበትን ጊዜ መናፈቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በተሰጣቸው ሥልጠና መሠረት ከፕላስቲክ የተሠሩ የእንሰት ማብለያዎችንና የማብላላት ሂደቱን የሚያፋጥነውን እርሾ በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማግኘት መቻላቸውን አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ማሽኖቹን በማዳረስ የሚጠቀሙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት