የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኮምፒውቲንግ እና የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ፋከልቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪና የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህር አስቻለው አረጋ ‹‹Cloud-Enabled Smart and Green Healthcare Information Service Model›› በሚል ርዕስ በጤና ተቋማት ላይ ያሉ አገልግሎቶችን ለማዘመን ያቀረቡት የምርምር ንድፈ ሃሳብ ግንቦት 23/2014 ዓ/ም ተገምግሟል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምር ንድፈ ሃሳብ አቅራቢው መምህር አስቻለው አረጋ ጥናታቸው ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የአገልግሎት ችግሮችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ መምህር አስቻለው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ላይ የታከመ ታካሚ ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ሪፈር በሚደረግበት ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ላይ ያለው መረጃ አጠቃላይ ሆስፒታል ላይም መገኘት መቻል አለበት፡፡ ይህም የታካሚውን መረጃ በድጋሚ እየጻፉ ጊዜ ማባከን፣ የታካሚውን የቀድሞ የሕመም ታሪክ ሳያውቁ መድኃኒት መስጠትና የመሳሰሉ ችግሮችን ይቀርፋል፡፡

ወጥ የሆነ የማዕከላዊ መረጃ አያያዝ ዘዴ መኖሩ አንድ ታካሚ የተለያዩ ቦታዎች ቢታከምም የሕክምና መረጃዎቹ በቀላሉ እንዲገኙና የተሻለ ሕክምና እንዲያገኝ ብሎም ታካሚው የራሱን መረጃ እንዲቆጣጠርና ለሐኪም ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥ የሚያደርግ መሆኑን ንድፈ ሃሳብ አቅራቢው ተናግረዋል፡፡ የምርምር ሥራቸው አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ በአርባ ምንጭ ድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና በአማሮ ልዩ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም መረጃዎችን በተግባር ለማጠናቀር ዝግጅት ላይ ነኝ ብለዋል፡፡

የጥናቱ አማካሪ ፕ/ር ዲፒ ሻርማ/DP Sharma/ እንደገለጹት የምርምር ንድፈ ሃሳቡ የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች የደንበኞቻቸውን አገልግሎት ለማሻሻል በጋራ መረጃ መለዋወጥ የሚችሉበትን መንገድ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ በኢትዮጵያ የጤና እንክብካቤ ዘርፍ ላይ ያተኮረው የምርምር ንድፈ ሃሳብ በበይነ-መረብ የተደገፈ መሆኑና በሀገር ውስጥ መሠራቱ የሚበረታታና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ብዙ ልምድ ሊያበረክት የሚችል መሆኑን አማካሪው ተናግረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደ መሆኑ 2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞችን በብዛት እየከፈተ እዲሁም የ3ኛ ዲግሪ የምርምር ንድፈ ሃሳቦች በስፋት እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም እንደ ኢንስቲትዩት የራሳችንን አሻራ የምናስቀምጥበትና ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎችም ራሳቸውን ለማሳደግ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ደረሰ ደመቀ በሰጠው አስተያየት በንድፈ ሃሳቡ የቀረበው የመረጃ አያያዝ ዘዴ በጤና ተቋማት የታካሚዎች ካርድ ቢጠፋ መረጃቸውን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ለሀገራችን የሕክምና ዘርፍ በእጅጉ ጠቃሚና በተግባር ተሠርቶ ለማየት የሚያጓጓ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት