በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ከፌዴራል፣ ከክልልና ከዞኑ ከመጡ ባለድርሻ ተቋማት አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እና ተመራማሪዎች ጋር ዘላቂ የትብብር ግንኙነት ሥራዎችን አብሮ መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ የጋራ ውይይት በቱሪስት ሆቴል ግንቦት 25/2014 ዓ.ም ተደርጓል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ፕሮግራሙ ትልቅ ዓላማ የያዘ እንደሆነ ገልፀው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተናቦ መሥራት ለሀገራችን ዕድገት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በምኅንድስናው ዘርፍ የተሰጠውን ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሀገር ልማት የማበርከት ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር መሥራቱ በተሻለ ሁኔታ በመማር ማስተማር፣ በምርምሩና በማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ውጤታማ እንደሚያደርግ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል ፡፡

በትብብር የመሥራት አስፈላጊነት፣ ከትብብር ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች፣ በቀጣይ በትብብር ሊሠሩ የሚችሉ ጉዳዮችና ምቹ ሁኔታዎች የመሳሰሉትን የውይይት ይዘቶች በተመለከተ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ገለጻ አቅርበዋል፡፡ እንደ ኢንስቲትዩት የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮና ራዕይ የማጠናከር ሚናውን ለመወጣት እንዲያስችለው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ ለተሻለ ለውጥ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነህ ኢንስቲትዩቱ በቀጣይነት የተለያዩ የትብብር ስምምነቶችን በመፈራረም በተለይ ከማሪታይም ባለሥልጣን መ/ቤትና ከሌሎችም ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጅት እያጠናቀቀ ነው ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የማኅበረሰቡን ችግር ከመቅረፍ አኳያና የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ለመለወጥ በተለያዩ ዘርፎች አብሮ መሥራት እንዲቻል እንዲሁም የተሻሉ አማራጭ የትብብር ሥራ ሃሳቦችን ኃላፊነት ከለባቸው አካላት ለማሰባሰብ መሰል ውይይት ትልቅ ግብዓት የሚገኝበትና ነው ብለዋል፡፡

ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ቱሪዝምን በሚመለከት ያሉንን ሀብቶች የመጠበቅ፣ የማጎልበት፣ የማሳደግና የማስተዋወቅ ሥራ በጋራ የሚሠራበት አቅጣጫ መያዙን ገልጸዋል፡፡ በሐይቆቹ ላይ ከዚህ በፊት ከአ/ምንጭ እስከ ዲላ የመርከብ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የተቋረጠ መሆኑን በማስታወስ ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ በመሥራት ለቱሪዝምና ለንግድ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠሩ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ ተ/ፕ/ በኃይሉ እንደገለጹት የቱሪዝም መረጃን የሚያቀላጥፍ መተግበሪያ እየተሠራ ሲሆን ይህም ተግባራዊ ሲሆን የአካባቢውን የቱሪዝም ዕድገትና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሻሽል ነው፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በምርምር ፕሮጀክቶችና በጋራ ሥራ አማራጮች ዙሪያ ገለጻ አቅርበዋል፡፡ በምርምር፣ ማኅበረሰብ አገልግሎት፣ መማር ማስተማር፣ በሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳዮች ላይ በመተባበር ለመሥራት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያለበት አካባቢ እንደ አካባቢ ከቆላ እስከ ደጋ የአየር ንብረት ያላቸው አከባቢዎች ያሉት በመሆኑ በግብርና ዘርፍ በሙዝ፣ አፕል፣ ማንጎ፣ ፓፓያና ሌሎች ፍራፍሬዎች፣ በሞሪንጋ፣ በዓሣ፣ በእንሰት፣ በጤና፣ በውሃ ምኅንድስና፣ በቱሪዝም፣ በኢንጅነሪንግ ቴክኖሎጂና በሌሎችም ጉዳዮች አብሮ ለመሥራት

ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ሀገር ለመድረስ ካሰብነው ግብ ላይ ለመድረስ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው ብቻውን ስኬታማ ለመሆን ስለማይችል ከሚመለከታቸው ተቋማትና ማኅበረሰቡ ጋር በጋራ መሥራቱ ውጤታማ እንደሚያደርግ በመገንዘብ ለትብብር ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከገለፃዎቹ ቀጥሎ በተካሄደው ውይይት ከተሳታፊዎች ዩኒቨርሲቲው የተለያየ ልምድ ካካበቱ ምሁራንና ተመራማሪዎች ለቀጣይ ሥራዎች ግብዓቶች ለማሰባሰብ የጀመረው ስትራቴጂ የሚበረታታ መሆኑን በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲውን ለተነሳሽነቱ አድንቀዋል፡፡ በውይይቱም የተለያዩ አስተያየቶችና ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሜካኒካልና ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኢንስቲትዩት የመጡት ፕሮፈሰር ዳንኤል ቅጣው ጋሞ ዞንና አካባቢው በዓባያና ጫሞ ሐይቆች፣ በእግዜር ድልድይ ተራራ፣ በነጭ ሣርና አካባቢው የደን ሽፋን፣ በምንጮቹ፣ በዓዞ እርባታና በሌሎችም መስሂቦች የታደለና በቱሪዝሙ ዘርፍ እምቅ ሀብት ያለው መሆኑን በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢው የቱሪዝም ቋት በመሆን የሥልጠናና የማማከር አገልግሎት የመስጠት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዳንኤል በኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ባላቸው የቦርድ ኃላፊነትም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን በመላክ በተግባር ከሚያውቁት ዕውቀት በተጨማሪ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲመለከቱ እንዲሁም ከተዘማጅ ኢንጂነሪንግ ዘርፎች ምሩቃንን እስከማስቀጠር በሚያስችል ደረጃ በጋራ ለመሥራት ትብብር እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የመጡት ካፒቴን ጌትነት ዓባይ በበኩላቸው መ/ቤታቸው የባሕር ላይ ሕይወትን፣ የመርከቦችንና ጀልባዎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራና በብሉ ኢኮኖሚ/Blue Economy/ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል፡፡ ካፒቴኑ የውሃ አካላት እንደ ሐይቆች፣ የጉድጓድ ውሃ፣ ወንዞች፣ ባሕርና ሌሎችም ያሉን እምቅ ኃይሎችን በመጠቀም ለሚቀጥለው ትውልድ ሳይጎዳ በማስተላለፍ ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ ጠቅሰው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከመሥሪያ ቤታቸው ጋር አብሮ መሥራት ይችላል ብለዋል፡፡ ካፒቴን ጌትነት በምኅንድስናው ዘርፍም ዩኒቨርሲቲው በብቃት አሠልጥኖ የሚያወጣቸውን የሜካኒካልና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎችን በማሪታይም ባለሥልጣን፣ በባሕር ላይና በውጭ ሀገር መርከቦች ላይ የማስቀጠር ሥራ በትብብር ሊሠራ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በውጭ ሀገር መርከቦች ላይ ምሩቃንን በማስቀጠር ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተሻለ ልምድ እንዳለው በማስታወስ ባለሥልጣኑ በቀጣይም 40 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎችን ለማስቀጠር ዕቅድ ይዞ እየሠራ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ጋርም የሚሄድ ስምምነት ማድረግ ይችላል ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሜካኒካልና ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኢንስቲትዩት የመጡት ፕሮፈሰር ዳንኤል ቅጣው፣ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪካል ኢንጂነርስ ሶሳይቲ የመጡት ዶ/ር ኢንጅነር ብርሃኑ ግዛው፣ ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የመጡት ካፒቴን ጌትነት ዓባይ፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ፣ ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች የመጡ እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት