አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን አካባቢ ጥበቃና ልማት ጽ/ቤት፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና ከGIZ-CLM /ጂ.አይ.ዘድ-ሲኤል.ኤም/ ጋር በመተባበር በዓለም ለ49ኛ በሀገራችን ለ29ኛ ጊዜ የተከበረውን የዓለም የአካባቢ ቀን ‹‹አንድ ምድር ብቻ! - ከተፈጥሮ ጋር በዘላቂነት ተስማምቶ መኖር!›› በሚል መሪ ቃል ግንቦት 27/2014 ዓ.ም አርባ ምንጭና አካባቢዋን በማጽዳት፣ ችግኝ በመትከልና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በደማቅ ሁኔታ አክብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በተፈጥሮ የተሰጠንን ምድርና ተፈጥሯዊ የሆኑ ሀብቶችን ጠብቆ ማቆየት ወሳኝ ሲሆን ምድርን በእንክብካቤና በጥንቃቄ መገልገል እንደሚገባ ጠቁመው ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን እንደ ዓለምም ሆነ እንደ ሀገር ትልቅ ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሬዝደንቱ ገለጻ የአየር ብክለትና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ተያያዥና ትኩረት የሚሹ በመሆኑ ለአረንጓዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ እንዲሁም የዓባያና ጫሞ ሐይቆች በደለል የመሞላት አደጋ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ምሁራንን በማሳተፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ የተደረገው የአካባቢ ጽዳትና የችግኝ ተከላ ንቅናቄም ከተሠራው ሥራ ይልቅ ማኅበረሰቡን ለቀጣይ ሥራ ለማነሳሳትና ለማበረታታት ቁልፍ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ቲቆ ትላንቴ አካባቢ ጥበቃ ለመኖር የሕልውና ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ዛፎችን በመትከልና አካባቢን በተገቢው ሁኔታ ጠብቆና ተንከባክቦ ማቆየት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በአየር ንብረትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮሩ በጥናትና ምርምር የተደገፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ያሉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቲቆ በተለይ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ ም/አስተዳዳሪው በሀገር ደረጃ ያለውን አዋጅ ተከትሎ በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ተግባራት አስመልክተው በመሬት መሸርሸር፣ በቆሻሻ አወጋገድና የሐይቆች በደለል መሞላት ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እየተሠሩ ያሉ ጅምር ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የሚሠሩ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ለተፋሰስ ሥራ የሚውሉ ችግኞችን፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ለከተማ ውበትና ጥላ የሚውሉ ዛፎችን ማፍላትና ማሰራጨት ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የተጎዱ ቦታዎች እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራ አበረታች ውጤት እንደታየበትና ለበርካታ ግለሰቦችም ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ተክሉ አክለውም አካባቢን ባላገናዘበና ባልተናበበ የመሬት አጠቃቀም ምክንያት የሚከሰተው የመሬት ናዳና መንሸራተት እንዲሁም ሳይንሳዊ ዳራውን ያልጠበቀ የቆሻሻ አወጋገድ በዓባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የሚያስከትለው የደለል መሙላት አደጋ ከባድ መሆኑን ጠቁመው ያለንን መሬት በጥንቃቄ መጠቀምና ተስማምቶ መኖር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮውም የአካባቢ ጥበቃ ቀን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወስዱና አሻራቸውን እንዲያኖሩ የሥራ ኃላፊነት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጸ/ቤት ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ይበልጣል ይሁኔ በበኩላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ በስምንት ወረዳዎች ስነ-ምኅዳሩን የሚመስሉ ስምንት የችግኝ ጣቢያዎች በማቋቋም ለዞኑም ሆነ ለወረዳዎቹ ትልቅ የችግኝ ግብዓት ማቅረብ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

የጋሞ ዞን ደን አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መዓዜ ሸከኔ እንደገለጹት የደረቁ ምንጮችንና የተጨፈጨፉ ደኖችን ለመመለስ በቅንጅት በመሥራት የምንኖርባት ምድር ለሕይወት ምቹ እንድትሆን በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር እንደሚገባ ተናግረዋል፡


የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ሁለንተናዊ ምልከታ እንደሚያስፈልግና ከደን ጥበቃ ጋር ተያይዥነት ያላቸው በጋሞ ባህል ውስጥ ያሉ እሴቶች ተጠንተው ጎልተው የሚወጡበትን ሂደት መፍጠር ለውጥ ለማምጣት አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ነባር መምህራንና ተመራማሪዎች በሆኑት በዶ/ር ስምዖን ሽብሩና በዶ/ር ፋሲል እሸቱ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በዕለቱም የጋሞ ዞን ም/አስተዳዳሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና ም/ፕሬዝደንቶች፣ ዳይሬክተሮች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮችና ዲኖች፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የGIZ-CLM ተወካዮች፣ ሌሎች ከአ/ም ከተማ አስተዳደርና ከጋሞ ዞን የተጋበዙ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት