የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ት/ክፍል ከአርባ ምንጭ መምህራን ማሠልጠኛ ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለኮሌጁ የአስተዳደር ሠራተኞች በየሥራ ጠባያቸው በመከፋፈል ከግንቦት 23-26/14 ዓ/ም በተቋማዊ ባህርይ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ወ/ሮ አስቴር ሰይፉ ዩኒቨርሲቲው በሥልጠናና በተለያዩ ሥራዎች ማኅበረሰቡን እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው አርባ ምንጭ መምህራን ማሠልጠኛ ትምህርት ኮሌጅ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ መምህራን ማሠልጠኛ ትምህርት ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዲን አቶ ያርቾ ያያ በበኩላቸው በተቋሙ ሠራተኞች የሚስተዋሉትን የዕውቀት፣ የአመለካከትና የክሂሎት ክፍተቶች ለመሙላት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ኮሌጁ ሥልጠናውን በየዓመቱ የመስጠት ዕቅድ እንዳለው የተናገሩት ዲኑ ከሥልጠናው በኋላ የመጡ ለውጦች በእያንዳንዱ የሥራ ሂደት ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ አቶ መላኩ በሻ እንደገለጹት ሥልጠናው በድርጅት ባህርይና በባህርዩ ላይ ተፅዕኖ በሚያሳድሩ የግለሰብ፣ የቡድንና የመዋቅር ባህርያት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከግለሰብ ባህርይ አንጻር ለሥራቸው አዎንታዊ አመለካከትን እንዲያዳብሩ የሥራ ቦታ አመለካከትና የሥራ ቦታ ስብዕና /Work Place Attitude & Work Place Personality/ ሥልጠና መሰጠቱን አቶ በሻ ተናግረዋል፡፡ የቡድን ባህርይን በተመለከተ የመሪነት ባህሪያት፣ የግጭት አፈታትና የመሳሰሉ ነጥቦች የተዳሰሱ ሲሆን ከመዋቅራዊ ባህርያት ውስጥ በዋናነት ጭንቀትን መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሠልጣኞች ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም እንዲኖራቸው ጠንቃቃ አለመሆን፣ በዕቅድ አለመመራት፣ ሥራን ማሳደር፣ ግድየለሽነትና የመሳሰሉ የጊዜ አጠቃቀም ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን አሠልጣኙ ገልጸዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል ወ/ሮ ኢትዮጵያ ኃይሉ እና አቶ ዘማች ደጀኔ በሰጡት አስተያየት ከመጠን በላይ መጨነቅና ያለ ዕቅድ መመራት በሥራ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እና በአንጻሩ ለሥራ ጥሩ አመለካከት መያዝ ያለውን በጎ አስተዋፅኦ ከሥልጠናው መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት