በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ስር በሚገኙ ሦስት ፋከልቲዎች የቀረቡ 7 የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች ግንቦት 29/2014 ዓ/ም የውጭ የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞችን ቁጥር በስፋትና በጥራት እየጨመረ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ኢንስቲትዩቱም የዩኒቨርሲቲውን ራዕይና ተልዕኮ ተከትሎ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞችን ለውጭ ግምገማ ማቅረቡ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈት ብቻ ሳይሆን በጥራቱም ላይ በዚያው ልክ መሥራት አለብን ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ ከውጭ ግምገማው አስፈላጊውን ግብዓት በመውሰድ ለተግባራዊነቱ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞቹ አውቶሞቲቭ ምኅንድስና፣ ኮምፒውተር ምኅንድስና፣ ኮምፒውተር ኔትዎርኪንግና ሴኪዩሪቲ፣ ኮንትሮልና ኢንስትሩሜንቴሽን ምኅንድስና፣ ሜታሎርጂና ማቴሪያል ሜታሎርጂ፣ ሜካኒካል ዲዛይን ምኅንድስና እና ሶፍትዌር ምኅንድስና መሆናቸውን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሞቹ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የውስጥ ግምገማ ያለፉ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት አግባብነታቸው ተረጋግጦ ለውጭ ግምገማ ቀርበዋል ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ሰሎሞን ንዋይ በበኩላቸው በተቀመጠው ሀገራዊ አቅጣጫ መሠረት በድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው ለግምገማ የቀረቡት ፕሮግራሞች ቀደም ሲል የነበሩንን 11 የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች ቁጥር ወደ 18 ከፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምኅንድስና ት/ክፍል ኃላፊና የሥርዓተ ትምህርቶቹ የውጭ ገምጋሚ ዶ/ር ልብሰወርቅ ነጋሽ የትምህርት ፕሮግራሞቹ ሀገራችን ወደ ኢንደስትሪው ዘርፍ ለማደግ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሞቹ በከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ መሠረት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የውስጥ ግምገማ የተደረገባቸው ሲሆን ለውጭ ግምገማው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኢንደስትሪ ዘርፍ እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ ከሰው ኃይልና ከቤተ-ሙከራ ጋር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በትብብር በመቅረፍ ወደ ተግባር እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት