በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አዘጋጅነት በሀገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት አስመልክቶ በተሠራ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ለት/ክፍሉ መምህራንና ለባለ ድርሻ አካላት ሰኔ 3/2014 ዓ/ም ትምህርታዊ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ዘውዴ አዳነ በቁልፍ ንግግራቸው የዜጎች የገቢ ሁኔታ ባልተሻሻለበት ግሽበት መከሰቱ ጫናውን ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረው ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ችግሩን ለመቀነስ የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመንደፍ ጥረቶች ቢደረጉም በሀገሪቱ የሚከሰቱ ተደራራቢ የውስጥና የውጭ ጫናዎችን መቅረፍ አልተቻለም ብለዋል፡፡ ድርቅ፣ የጸጥታ ሁኔታ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም፣ የኮሮና ቫይረስና መሰል ችግሮችን ለመቋቋም የሚደረጉ የባንክ ብድሮች የዋጋ ግሽበትን ያባባሱ መሆኑን አቶ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡ የጥናቱ ውጤት እና ከምሁራን የተሰጠው ጥያቄና አስተያየት በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ዕይታን የሚፈጥር ነው ያሉት አማካሪው የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች የተነሱበትና የመንግሥትን እርምጃዎች ያመላከተ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ከፍተኛ ተመራማሪና ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ዶ/ር አረጋ ሹመቴ ጥናቱ የዋጋ ግሽበትን ያስቀጠሉ ምክንያቶችና የፖሊሲ ሃሳቦች ምንነት ላይ ማተኮሩን ገልጸዋል፡፡ ከፍ ያለ የገንዘብ መጠን ወደ ኢኮኖሚው መለቀቅ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ወጪ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነት አለመጨመር፣ የኢንደስትሪ ምርት በሚፈለገው መጠን አለማደግ እና በአምራችና በሻጮች መካከል ያሉ ጣልቃ ገቦችና ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ከዋጋ ግሽበቱ ምክንያቶች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠር የዋጋ ግሽበትን የሚቆጣጠር አቅም፣ ዕውቀትና ሙሉ ሥልጣን ያለው ተቋም አቋቁሞ ክትትል ማድረግ እና የውጭ ምንዛሪን ወሳኝ ለሆኑ ጉዳዮች መጠቀም በጥናቱ እንደ አጭር ጊዜ የመፍትሄ ሃሳብ የቀረቡ ሲሆን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የመሬትና የግብዓት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ ፈጠራና የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል በረዥም ጊዜ ዕቅድ ሊያዙ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የዋጋ ግሽበት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መሠረታዊ ችግር በመሆኑ መፍትሄ ለማምጣት መሥራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ከምግብና ከጤና ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ሳይንሳዊ ከሆነ ማኅበረሰብ ጋር የሚደረግ መስተጋብር ጠቃሚ የውሳኔ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለሚመለከተው አካል ለማድረስ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ በበኩላቸው የዋጋ ግሽበት ለሁሉም ዜጋ ችግርና ፈተና እንደሆነ ገልጸው በተለይ ታችኛው የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉት ለእለት ጉርስ ጭምር አዳጋች መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡ የጥቁር ገበያ መስፋፋትና የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየት ችግሩን ማባባሱን ጠቅሰው መፍትሄ ለማበጀት የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና መንግሥት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የኮሌጁ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ተክለብርሃን ዓለምነህ በመድረኩ የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ መደረጉንና ዩኒቨርሲቲው ከኢኮኖሚክስ ማኅበር ጋር ተቀራርቦ እንዲሠራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ በአጥኚዎችና በፖሊሲ አውጪዎች መካከል ያለውን ክፍተት ማጣጣም እንደሚገባ የጠቆመ መድረክ ነውም ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመዝጊያ ንግግራቸው በዋጋ ግሽበትና መፍትሄዎቹ ላይ መነጋገር ሁሉም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ምሁራን ሳይንሳዊ ምርምሮችን መሥራትና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር እና ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የመጡ ተጋባዥ እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችና ሌሎችም ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን ለፖሊሲ አቅጣጫ የሚውሉ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት