የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ከጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ከዞኑና ከተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ ወጣት አደረጃጀቶች ከሰኔ 7-10/2014 ዓ/ም የሚቆይ የፈሳሽና ደረቅ ሳሙና አዘገጃጀት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ሥልጠናው ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት የሆኑትን ኢንተርፕራይዞች አቅም ለመገንባት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሥራና የማስተዳደር ክሂሎት አለመኖር እና የገንዘብ አቅም እጥረት የኢንተርፕራይዞች ተግዳሮቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ዲኑ ተግዳሮቶቹን በማለፍ ሥራ አጥነትን ለመቀነስና ኢኮኖሚን ለማሳደግ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለሠልጣኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ኮሌጁ ሥልጠናዎችን በመስጠት የክሂሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም በበኩላቸው ኮሌጁ በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የተለያዩ ጥናቶች፣ የልማት ሥራዎች፣ የሥልጠናና የማማከር አገልግሎቶች፣ የጎልማሶች ትምህርትና ሌሎችም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የፈሳሽና ደረቅ ሳሙና ምርት አዘገጃጀት ምርምርን መነሻ አድርጎ ወደ ማኅበረሰቡ የተሸጋገረ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኬሚስትሪ ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ ነብዩ ጫሊ በቤት ውስጥ የሚዘጋጅ ደረቅ ሳሙና ከእንስሳት ስብ፣ የወይራ ዘይት፣ ሬት፣ አልኮል፣ አፈርና ኮስቲክ ሶዳ/Caustic Soda/ ንጥረ ነገሮች የሚሠራና በትንሽ ካፒታል የሚጀመር የሥራ ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡ ለቀለም እርድ እና ለሽታ የሎሚ ቅጠል በመጨመር መሥራት እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ኢያሱ በዞኑ በኢንተርፕራይዝ ዘርፍ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙና ሥልጠናውም የዚህ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው በቀላሉ በሚገኙ ንጥረ ነገሮች ሳሙና ማምረት የሚችሉበትን ዕውቀት ከሥልጠናው ማግኘታቸውንና ክሂሎቱን ተጠቅመው ለቤት ውስጥ አገልግሎትም ሆነ ለገቢ ማስገኛ ሥራ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የደረቅና ፈሳሽ ሳሙና መሥሪያ ኬሚካሎችንና ማሽኖችን በመግዛት ተምረው ወደ ሥራ ያልተሰማሩና በማኅበራት የሚደራጁ ወጣቶችን ለመደገፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት