የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ከምርምር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ‹‹Manuscript Writing››፣ ‹‹Grant and Collaborative Proposal Writing››፣ ‹‹Digital Data Collection››፣ ‹‹Opportunities for Collaborative Projects›› በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ሴት ተመራማሪዎችና መምህራን ከሰኔ 10-11/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት የሴት ተመራማሪዎች ተሳትፎ ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር መሻሻል ያሳየ ቢሆንም በሴት ተመራማሪዎች ቁጥር ላይ አሁንም መዋዠቅ ይስተዋላል፡፡ ሥልጠናው ሴት ተመራማሪዎች ልምድ ካላቸው ነባር ተመራማሪዎች ተሞክሮን የሚያገኙበትና ለምርምር ሥራቸው ድጋፍ የሚሆናቸው ነው ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሠናይት ሳህሌ ሴቶችን ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ላይ ማሳተፍ ከታች ጀምሮ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ከመለወጥ አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረው በቀጣይ በት/ክፍሎች በመከፋፈል ሰፋ ያለ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹Opportunities for Collaborative Projects›› በሚል ርዕስ ሥልጠና የሰጡት የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማሪያም ሴት ተመራማሪዎች በአምስቱ የምርምር ዓይነቶች፡- ‹‹Small Scale Research››፣ ‹‹Special Females Research››፣ ‹‹Grand Project›› እና ‹‹Young Research›› የመሳተፍ ዕድል እንዳላቸውና የበጀት ድጋፍ እንደሚያገኙም ተናግረዋል፡፡

የኮምፕዩቲንግና ሶፍትዌር ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና አሠልጣኝ አልአዛር ባሕሩ በበኩላቸው ዲጂታል መረጃ አሰባሰብን አስመልክቶ ሥልጠናው ተመራማሪዎች ሞባይል ስልክና ታብሌቶችን ተጠቅመው ያለ ኢንተርኔት መረጃን መሰብሰብ፣ መጠይቆችን ማዘጋጀት፣ ማሰራጨትና ለምርምር ውጤቶች መጠቀም የሚችሉበትን መንገድ ያካተተ ነው ብለዋል፡፡ ሀገር ውስጥ እያደገ ያለው የኢንተርኔት ሽፋን መረጃ በወረቀት መሰብሰብን የሚያስቀርና ተመራማሪዎች ትክክለኛውን እውነታ የሚገልጽ ጥራት ያለው ምርምር እንዲሠሩ እንደሚያደርግም አሠልጣኙ ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት