በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ትብብር በኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት አማካኝነት የተሠሩ 4 ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በ 1 የፈጠራ ሥራቸው ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የአእምሯዊ ንብረት ማረጋገጫ /Patent/ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡

ከፊል አውቶማቲክ የእንሰት መፋቂያ ማሽን፣ በሞተር የሚሠራ የእንሰት አሚቾ መፍጫ ማሽን፣ የእንሰት ማብላያ እንስራ ፈጠራዎችና ከተብላላ እንሰት የሚዘጋጅ የቆጮ ዱቄት አዘገጃጀት ዘዴ የጋራ የአእምሯዊ ንብረት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያገኙ ሲሆን ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ የቆጮ ማብላላት ሂደትን በሚያፋጥን እርሾ /Starter/ ፈጠራቸው በግል የአእምሯዊ ንብረት ማረጋገጫውን እንዳገኙ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአእምሯዊ ንብረት ማረጋገጫው የዩኒቨርሲቲውን ገጽታና ደረጃ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ቶሌራ ቴክኖሎጂዎቹ የባለቤትነት ማረጋገጫ ከሌላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወደ ማኅበረሰቡ የማሸጋገር ሥራ ውስጥ ደፍረው የማይገቡ በመሆኑ የባለቤትነት ማረጋገጫው የተቋማትን በትብብር የመሥራት ፍላጎት በእጅጉ የጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን እንሰት አምራች በሆኑ የሀገራችን ክፍሎች ለማዳረስ ብሎም እንሰትን የዩኒቨርሲቲው መለያ/Brand/ ለማድረግ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ቶሌራ ጠቁመዋል፡፡

እንሰት ድርቅን የሚቋቋም፣ በትንሽ ቦታ ብዙ ምርት መስጠት የሚችልና በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን ሕዝብ በላይ በዋና ምግብነት የሚጠቀምበት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ተክል ነው፡፡ የእንሰት ምርትና የማብላላት ሂደትን ለማዘመን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ጥረት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ሚና የሚያበረክት እንደመሆኑ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ከዩኒቨርሲቲው ጎን ሊቆሙና ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት