ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የትውውቅ እንዲሁም ለቀድሞ የቦርዱ አባላት የምስጋናና የሽኝት መርሃ ግብር ሰኔ 11/2014 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የቀድሞ የቦርድ አባላት ዩኒቨርሲቲውን ሲያገለግሉ በቆዩበት የሥራ ጊዜያቸው ላበረከቷቸው በርካታ ጠቃሚ ነገሮች ምስጋና ለማቅረብ፣ ልምዳቸውን ለአዲስ አባላት እንዲያጋሩ እንዲሁም ትኩረት በሚፈልጉ ቀሪ ሥራዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተዘጋጀ መርሃ ግብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ቦርዱ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያገለግሉ የቆዩ አባላት ሽኝት ያካሄደ ሲሆን በቀጣይ ለ2 ዓመት ቦርዱን እንዲያገለግሉ ከተሰየሙ አባላት ጋር ትውውቅ አድርጓል፡፡  

በዚህም መሠረት የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የቦርዱ ሰብሳቢ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ የአባይ ባንክ ፕሬዝደንት አቶ ዮሐንስ ገሰሰ፣ የፕሮፌሰሮች ካውንስል አባል ፕሮፈሴር ይልማ ስለሺ፣ የፕሮፌሰሮች ካውንስል አባል ፕሮፌሰር ኢታና ደበሌ እና የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ የቦርዱ አባላት ሆነው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው፣ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ፈጠነ ተሾመ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክና ሥራ አመራር ዳይሬክተር ጄኔራል ከበደ ግዛው ተሰናባች የቦርድ አባላት ናቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1979 ዓ/ም ጀምሮ ይሰጡ የነበሩ የትምህርት መስኮች፣ የመምህራን፣ የተማሪዎችና የተመራማሪዎች መረጃ፣ ሲከናወኑ የነበሩ ምርምሮችንና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን ጨምሮ እስከ 2014 ዓ/ም ድረስ ያለውን አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው እንቅስቃሴ የተመለከተ መረጃ ቀርቧል፡፡ በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ከቦርዱ ለተሰናበቱ የቀድሞ አባላት የምስክር ወረቀትና የምስጋና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሸን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት