የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ለቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ተመራቂ ተማሪዎች በሥነ-ምግባርና በሙስና ወንጀሎች ዙሪያ ሰኔ 20/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

በሥልጠናው የሥነ-ምግባር ጽንሰ ሃሳብ ምንነትና አስፈላጊነት፣ የሥነ-ምግባር ዘርፎች፣ የሥነ-ምግባር መርሆዎች፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ችግሮች፣ ሥነ-ምግባራዊ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያስችሉ መንገዶችና መሰል ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና አሠልጣኝ አቶ ዮሐንስ ዳና መሰል ሥልጠናዎች በየዓመቱ ለአዲስ ተቀጣሪ ሠራተኞችና ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች እንደሚሰጡ አስታውሰው ከዩኒቨርሲቲው የሚመረቁ ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል በማዳበር እና ሕግና ደንብን በማክበር ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ሥልጠናው ለተመራቂ ተማሪዎች መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዮሐንስ የሙስናና ብልሹ አሠራር መስፋፋት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች ላይ ተጽዕኖ ለመከላከል የሙስና ምንጭ በሆነው የሥነ-ምግባር ጉድለት ላይ ትኩረት አድርጎ በሥልጠናዎች ግንዛቤን ማሳደግ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው ተማሪዎች በተቋሙ በሚኖራቸው ቆይታ ከሚያገኙት የቀለም ዕውቀት ባሻገር ሥልጠናው ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ በሥነ-ምግባር ታንጸው የተማሩትን በተግባር እንዲያውሉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን ሥነ-ምግባር የሕይወት አቅጣጫ መሪ መሆኑን ገልጸው ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውድቀት መንስኤ የሆነውን ሙስናና የሥነ-ምግባር ግድፈት ለመታገል ተመራቂ ተማሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማለም ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት