የአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከ‹‹UNDP›› ፕሮግራም ጋር በመተባበር ከከተማዋ የተወጣጡ ወጣቶች ባቀረቡት የሥራ ፈጠራ ላይ ሰኔ 23/2014 ዓ/ም ውድድር አካሂዷል፡፡ ውድድሩ በጽንሰ ሃሳብ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን የተወሰኑት በተግባር የተደገፉ ማሳያዎችን አቅርበዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ለውድድር ከቀረቡ የ10 ማኅበራት የፈጠራ ሥራዎች መካከል የጸረ ተባይ መድኃኒቶች መርጫ ዘመናዊ ማሽን፣ ከሙዝ ግንድ የሚሠሩ አልባሳትና ለማሸጊያነት የሚውሉ የወረቀት ምርቶች፣ ከሙዝ የተመረተ ቺፕስ እና ከሚወገዱ ቁሶች የተመረቱ የማገዶ ምርቶች ይገኙበታል፡፡

የዩኒቨርሲቲ- ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዜጎች ሥራ ፈላጊ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ይህን እውን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ለ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ለተመራቂ ተማሪዎች፣ ለሥራ አጥ ወጣቶችና ለኢንተርፕራይዞች ተከታታይ የሥራ ፈጠራ ክሂሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ክትትል በማድረግና በመሸለም በከተማዋ ከሚገኙ የሥራ ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ጋር በጋራ መሠራቱ ሥራውን ስኬታማ ከማድረጉ ባሻገር ሥራ አጥነትን ለመቀነስና ለሀገር ኢኮኖሚ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ዩኒቨርሲቲው ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ባለው ተነሳሽነት ለተማሪው እንዲሁም ለማኅበረሰቡ የማማከርና ሥልጠና ድጋፎችን ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር የከተማውን ወጣቶች ለማበረታታት ባለው ዕቅድ መሠረት መርሃ ግብሩን በጋራ ለማዘጋጀት ችለናል ብለዋል፡፡ በቀጣይ በውድድሩ አሸናፊ ከሆኑ ወጣቶች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ዶ/ር ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡

ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በማበረታታት በገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቀነስና ከፈጠራ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለሌሎች በማሸጋገር የሥራ እድል ለመፍጠር በር እንዲከፍት የውድድርና የሽልማት መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱን የአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዱቡሻ አወቀ ገልጸዋል፡፡ ለስኬቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በውድድሩ ዜብራ የወረቀት ማምረቻ፣ ሀገሬ ባናና ቺፕስ እና ባይራ ባዮ ማስ ከ1ኛ-3ኛ የወጡ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲውና ከኢንተርፕራይዞች የገንዘብ ሽልማትና የዕውቅና ምስክር ወረቀት እንዲሁም ለሌሎች ተወዳዳሪዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ተሸላሚ ወጣት ሚካኤል ተስፋዬ ከሙዝ ግንድ ለማሸጊያነት የሚውል ወረቀት እንዳመረተና ባገኘው ሽልማት መደሰቱን ገልጾ በቀጣይ ለሚኖረኝ ሥራ የሞራል ስንቅ ሆኖኛል ብሏል፡፡ ሥራው ድጋፍ ቢደረግለት ወደ ትልቅ ኢንደስትሪ ማደግ የሚችል፣ ለብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥርና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚኖረው እንደሆነ ተናግሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖለጂ ሽግግር ዳሬክቶሬት፣ ከዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል፣ ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ የሥራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ እና ከከተማው የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ውድድሩ ፍትሐዊ እንዲሆን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲውና ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተመረጡ መምህራን በዳኝነት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት