በኢትዮጵያ የኢንዶኔዢያ አምባሳደር አል ቡስራ ባስኑር (Al Busyra Basnur) በግብርናው ዘርፍ በተለይ እምቦጭን ከመከላከልና የአኩሪ አተር ምርትን ከማሻሻል ጋር በተያያዘ የሀገራቸውን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰኔ 23/2014 ዓ/ም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ እምቦጭ የውሃ ውስጥ አካላት በተፈለገው መጠን በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት ምግብ እንዳያገኙ ተፅዕኖ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህም የዓሣ ምርት እንዳይጨምር አድርጎታል ብለዋል፡፡

የ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች እምቦጭ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመከላከልና አረሙ ለፍየል፣ ለበጎችና ለከብቶች ምግብነት እና ለተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት እንዲውል ትኩረት አድርገው የምርምር ጽሑፋቸውን እየሠሩ መሆኑን ዲኑ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ምርምሮቹ ውጤታማ ከሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን ማዳበሪያ በማስቀረት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ መሠረት ይሆናል፡፡

በዕለቱ በውሃ አካላት ላይ እምቦጭ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመከላከል እሴት ተጨምሮበት ለተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች መሥሪያነት ማዋል እንዲሁም የአኩሪ አተር ዝርያን ማሻሻል በሚቻልበት መንገድ ላይ በምስል የተደገፈ ውጤታማ የምርምር ሥራ በተሞክሮነት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በኢንዶኔዢያ ከዚህ ቀደም ለአርሶ አደሩና ለመንግሥት ፈተና ከነበረው እምቦጭ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ኮፍያና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሥራት ለተለያዩ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ይህንን ተሞክሮ በሀገራችንና በኮሌጁ ለማስተዋወቅ በቀጣዩ ዓመት መስከረም ወር ላይ ከኢንዶኔዢያ የዘርፉ ባለሙያዎች መጥተው ሥልጠና እንዲሰጡ መታቀዱ እና የአምባሳደሩ ጉብኝትም ለቀጣይ ሥራዎች የትውውቅ መርሃ ግብር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪዎችና በዘርፉ የሚሠሩ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመርሃ ግብሩ ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት