አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት/GIZ/ እና ከጀርመን ደን ልማት አገልግሎት አማካሪ ድርጅት ጋር በመተባበር ከጋሞ ዞን ለተወጣጡ 17 የደን እና የደን ጥበቃ ባለሙያዎች እንዲሁም ከማኅበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ለተወጣጡ መምህራን ከሰኔ 27 - ሐምሌ 1/2014 ዓ/ም የደን መሬትን ለመቆጣጠር በሚያስችሉ ሶፍትዌሮች አጠቃቀም ላይ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በኮሌጁ የጂኦግራፊ ት/ክፍል የGIS ባለሙያና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ‹‹Forest for Future Project›› አባል የሆኑት መምህር ኃይለማርያም አጥናፉ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ በደን፣ በደን ጥበቃ እና በግብርናና ጂኦ ኢንፎርሜሽን ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች በሳተላይት፣ በድሮን ቴክኖሎጂ እንዲሁም የመስክ ምልከታን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው የደን መሬት ቁጥጥር ሥርዓትን በመዘርጋትና በመጠቀም ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል የ‹‹GIS & Remote Sensing›› መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አስናቀ መኩሪያው በሰጡት ሥልጠና ለእርሻ፣ ለግጦሽ፣ ለሠፈራ እንዲሁም ለፍራፍሬ ልማት ምቹ የሆኑ ቦታዎችን በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ትክክለኛ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድና ትግበራ አዘጋጅቶ መሬት ላይ ማውረድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ይህም የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል፡፡ ዶ/ር አስናቀ በደለልና በደን ምንጣሮ ምክንያት እየተጎዱ ያሉ አካባቢዎችን ወደ ነበሩበት መመለስ አለመመለሳቸውን ምስለ መሬትን በመጠቀም አሳይተዋል፡፡

ባሕር ዳር ከሚገኘው የጀርመን ደን ልማት አገልግሎት አማካሪ ድርጅት የመጡት አቶ አዲስዓለም አሰፋ የድሮን ቴክኖሎጂ ሰው በቀላሉ ሊደርስባቸው በማይችሉ አስቸጋሪ ቦታዎች በአጭር ጊዜ፣ በቀላሉና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ለመሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎ በጂፒኤስ(GPS)የተሰበሰበውን መረጃ በመጠቀም ካርታ መሥራትን በተመለከተ እንዲሁም በድሮን የተሠራው በሰው ከተሰበሰበው ጋር ዝምድና ያለው ስለመሆኑ ሠልጣኞች በተግባር እንዲያረጋግጡና የደን ሀብት ያለውን ለውጥ በዘመናዊ መልክ ለማየት የድሮን ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሥራት እንደሚቻል መስክ በመሄድ በጂፒኤስ እንዲያረጋግጡ መደረጉን አቶ አዲስዓለም ገልጸዋል፡፡

የ‹‹Remote Sensing Solution/RSS/›› አማካሪ አልሪክ ኖከር (Ulrike Nocker) ደግሞ ‹‹ኮቦ ቱልቦክስ/KoBo Toolbox/›› የተሰኘውን የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ አሠልጥነዋል፡፡ በተጨማሪም አማካሪዋ በሰጡት ሥልጠና ‹‹Q GIS›› እና ‹‹ArcGIS›› አጠቃቀም ተካቷል፡፡

ሥልጠናው በሳተላይት፣ በድሮንና በሰው የተሰበሰበን መረጃ በማቀናጀት በተጨባጭ ያለውን ትክክለኛ መረጃ ማግኘት የሚቻልበትን ዕውቀት ያገኙበት እንዲሁም ከተለያዩ ሶፍትዌሮች ጋር ያስተዋወቃቸው መሆኑን ሠልጣኞች ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት