የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት KG-3 ያጠናቀቁ ሕፃናትን ለ24ኛ ጊዜ ሐምሌ 2/2014 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የአንድ ሀገር እድገት የሚወሰነው ባሏት የተማሩ ሰዎችና በሚያደርጉት አበርክቶ እንደሆነ ተናግረው የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ከመንግሥት ት/ቤቶች ባሻገር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በቅድመ-መደበኛ፣ በመደበኛና በከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ላለፉት 24 ዓመታት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ለስኬቱም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እንዲሁም የት/ቤቱ መምህራንና ወላጆች ትልቁን ሚና እንደተጫወቱ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና ሀገር ተረካቢ ሕፃናትን ተንከባክቦ ማሳደግና ማስተማር የወላጅ፣ የኅብረተሰቡና የመንግሥት ኃላፊነት እንደመሆኑ ት/ቤቱ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ዘንድሮ ለ24ኛ ጊዜ 47 ወንድ እና 48 ሴት በድምሩ 95 ሕፃናትን አስመርቆ ወደ 1ኛ ክፍል መሸኘቱን ገልጸዋል፡፡

የት/ቤቱ ቤት ርዕሰ መምህርት ወ/ሪት ሳራ ጎይዳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ርቆ በመገኘቱ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞችን ለማገልገል ት/ቤቱ በ1994 ዓ/ም በ1 ሴክሽን፣ በ27 ተማሪዎችና በ1 መምህርት መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋናው ግቢና በአባያ ካምፓስ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በ2015 ዓ/ም በኩልፎ ካምፓስ ማቆያ ለመክፈት ዝግጅት መጠናቀቁንና በቀጣይም በሁሉም ካምፓሶች ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ወ/ሪት ሳራ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የወላጆች አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ሊያውቁ የሚገባቸውን እያሳዩ፣ በሃሳብ እየገሩና መንገድ እየመሩ ሙሉ ሰብዕና ያለው ትውልድ ሆነው እንዲያድጉ ሊረዷቸው እንደሚገባ በመርሃ-ግብሩ ተመላክቷል፡፡

በእለቱ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ፣ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና፣ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህርት ወ/ሪት ሳራ ጎይዳ፣ የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገዳሙ ጌታቸው፣ የወላጅ ኮሚቴ አባላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆች የታደሙ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ግጥሞች፣ ትምህርታዊ ውድድሮችና ፋሽን ሾው በተማሪዎች ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም ከየክፍሉ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት