በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ሥር የግራንትና ኮላቦሬቲቭ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት /Grant and Collaborative Project Management Directorate/ መቋቋሙ ተገለጸ፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲነጻጸር ያሉት የትብብር ፕሮጀክቶች ቁጥር አናሳ መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲውን የትብብር ፕሮጀክቶች ቋት በማድረግ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ዳይሬክቶሬቱ መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡ የትብብር ፕሮጀክቶች የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማብቃት እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የምርምር ቤተ-ሙከራዎችንና የመስክ ምልከታ ጣቢያዎችን ለማቋቋም ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ዳይሬክተሩ ተናግረው በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ፕሮጀክቶችን ቀርጸው ድጋፍ ቢያገኙ በርካታ ጥቅሞችን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡

ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ተቋማትና ኢንደስትሪዎች ጋር በመተባበር ፕሮጀክቶች እንዲቀረጹ መምህራንን በመደገፍ፣ የፕሮጀክት ድጋፍ ጥሪዎችን በማሰስ ለመምህራን ተደራሽ በማድረግ እና የገንዘብ ምንጮች እንዲገኙ በማስቻል ዩኒቨርሲቲው መልካም የፕሮጀክት አፈፃፀም እንዲኖረው ማድረግ የዳይሬክቶሬቱ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የፕሮጀክት ጥሪዎችን ለማሸነፍ ከሚያስችሉ ሁኔታዎች መካከል እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራትን ብቻ የሚመለከቱ በርካታ የፕሮጀክትና የትምህርት እድል ጥሪዎች መኖራቸው አንዱ ሲሆን ይህም ለመምህራንና ለተመራማሪዎች ጉዳዩን ምቹ አጋጣሚ እንደሚያደርገው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከሀገሪቱ የመጀመሪያ ትውልድ ብሎም ከምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑ ለድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች ማስተማሪያ ፕሮጀክቶችን ለመንደፍ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በውሃ እና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች ለምርምር ሥራ የሚሆኑ ጣቢያዎች በአርባ ምንጭ፣ ዶርዜ፣ ግርጫ፣ እና ቦንኬ አካባቢዎች ያሉት መሆኑ ለማስተማሪያ፣ ለምርምርና ለማኅበረሰብ ጉድኝት ከማዋል ባሻር ለፕሮጀክት ቀረጻ ወሳኝ ግብዓት በመሆን እንደሚያገለግሉ ዶ/ር ቶማስ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ የፕሮጀክት ጥሪ ከሚያደርጉ ከ4 ሺህ በላይ ተቋማት የትምህርት፣ የምርምር፣ የጉዞ ወዘተ መረጃዎችን በመሰብሰብ በአንድ ቋት ከሚያስቀምጠው ‹‹Research Beeline›› የተሰኘ ድርጅት ጋር ዩኒቨርሲቲው ስምምነት በመፍጠር የ1 ዓመት ውል ተፈራርሞ ክፍያ የፈፀመ ሲሆን አሁን ላይ ከ300 በላይ መምህራን የመረጃ ቋቱን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም መምህራን የምርምር ንድፈ ሃሳብ ጥሪዎችን ለማግኘት ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠረላቸው በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ኢ-ሜይል ብቻ በመመዝገብ የ‹‹Research Beeline›› የመረጃ ቋትን መጠቀም እንደሚችሉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በማንኛውም ሰዓት የምርምር ጥሪ ያለ በመሆኑ መምህራን በዩኒቨርሲቲ፣ በኮሌጅ/ኢንስቲትዩት፣ በት/ክፍል እንዲሁም ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገራት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፕሮጀክቶችን ቀርጸው መወዳደር እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ልምድ ያላቸውን የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገራት ምሁራንን በመጋበዝ የተሻለ ሥልጠና እና የአቅም ማጎልበቻ ድጋፎችን በማድረግ ፕሮጀክቶችን ለመቅረጽ እንዲችሉ እንደሚመቻች ዳይሬክተሩ

ተናግረዋል፡፡ መምህራን የፕሮጀክት ጥሪ አግኝተው ንድፈ ሃሳብ መጻፍ ቢፈልጉ የፕሮጀክት ዕቅዳቸው ተገምግሞ የ‹‹Seed Fund›› እድል ተጠቅመው አስፈላጊ መረጃ ለመሰብሰብና ለመሰል ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ ማግኘት እንደሚችሉ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ለአጋር ድርጅቶች በሚላኩበት ወቅት ከዩኒቨርሲቲው ድጋፎች ቢያስፈልጉ የሚጠበቀውን መረጃ ዳይሬክቶሬቱ ለመምህራን ምቹ እንደሚያደርግ እንዲሁም መምህራን የፕሮጀክት በጀት በሚሠሩበት ጊዜ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ‹‹Overhead Cost›› የመሳሰሉ አሠራሮች ምክርና ሃሳብ የሚሰጥ መሆኑን ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት