የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕንፃና ከተማ ፕላን ፋከልቲ ሕንድ ሀገር ከሚገኘው ‹‹ላቭሊ ፕሮፌሽናል ዩኒቨርሲቲ /Lovely Professional University›› ጋር በመተባበር ለፋከልቲው የ5ኛ ዓመት ተማሪዎች የምርምር ምንነት፣ አሠራር፣ አጻጻፍና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሐምሌ 01/2014 ዓ/ም የበይነ መረብ ገለጻ ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የፋከልቲው ዲን አቶ ገረመው ገ/ማርያም ከላቭሊ ፕሮፌሽናል ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙ መሆኑን ገልጸው የሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች በአካል ብቻ ሳይሆን በበይነ መረብ የዕውቀት ልውውጥ እንዲያደርጉ የኦንላይን ገለጻው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዲኑ ገለጻ ለመጀመሪ ጊዜ በተዘጋጀው ገለጻ የ5ኛ ዓመት ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፋቸውንና የተለያዩ ምርምሮችን ለመሥራት የሚረዳቸውን ግብዓት አግኝተዋል፡፡ በሂደቱ ተማሪዎች ጥያቄዎቻቸውን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ያገኙ ሲሆን ይህም ቀልጣፋ የሁለትዮሽ መስተጋብር ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ዲኑ አክለውም በቀጣይም በምርምርና በድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት መምህራን ሕንድ ሀገር ሄደው ከመማር ባሻገር መሰል የበይነ መረብ መርሃ ግብሮች እንደሚመቻቹ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት