የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለጨንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሰኔ 28/2014 ዓ/ም የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ቺፍ አካዳሚክ ዳይሬክተርና የቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተክሉ ተሾመ እንደገለጹት ለሆስፒታሉ አንድ ሚሊየን ብር የሚያወጡ ለልብ ምርመራና አጠቃላይ የታካሚውን የጤና ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችሉ ‹‹Patient Monitor››፣ ‹‹SG›› እና ‹‹CTG›› ማሽኖች ተበርክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በአቅራቢያው ያሉ ሆስፒታሎችንና ጤና ጣቢያዎችን በመደገፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ተክሉ ይህም የጤና ተቋማቱ ለማኅበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ተማሪዎቻችን የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የጨንቻ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘካሪያስ መንግሥቱ በበኩላቸው የቁሳቁስ ድጋፉ ታካሚዎች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ሌላ ቦታ በመጓጓዝ የሚያወጡትን ተጨማሪ ወጪና እንግልት የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጨንቻ ሆስፒታል ለበርካታ ኅብረተሰብ አገልግሎት ከመስጠቱ አንፃር ዩኒቨርሲቲው የሚያደርጋቸው ድጋፎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆኑን ዶ/ር ዘካሪያስ ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት