የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ትቤት የ2014 ዓ/ም የወላጆች ቀን በዓልን ሐምሌ 9/2014 ዓ/ም አክብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በዓለማችን ትልቅ አቅም ያለው መሣሪያ ትምህርት መሆኑን ገልጸው አእምሮን ከማሳደግ ባለፈ ማኅበራዊ ተግባቦታችንን እንድናሻሽል ስለ ጊዜና ሁለንተናዊ አመራር ዕውቀት ያስጨብጠናል ብለዋል፡፡

የላቀ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች መሸለማቸው በቀጣይ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያበረታታ መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ በተለይም ሴት ተማሪዎች ከፍ እያሉ ሲሄዱ ውጤታቸው እንዳያሽቆለቁል ወላጆች ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የት/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና የዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት ሀገር አቀፉን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተከትሎ ት/ቤቱ የተማሪ ውጤትና ሥነ-ምግባርን ለማሻሻል እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የት/ቤቱ ማኅበረሰብና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

የት/ቤቱ ወላጅ-መምህር ኅብረት ሰብሳቢ አቶ ገዳሙ ጌታቸው በትምህርት ዘመኑ የ2013 ዓ/ም ውጤትን መነሻ በማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመረሮች፣ ከትምህርት ቤቱ ቦርድና ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ከKG-11ኛ ክፍል ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በአንዳንድ ተማሪዎችና መምህራን ላይ የሚስተዋሉ የባህርይ ችግሮችን ለመቅረፍ ከዩኒቨርሲቲው ሥነ-ባህርይ ት/ክፍል ጋር በመቀናጀት ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን የጠቀሱት አቶ ገዳሙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የክረምቱን መግባት ተከትሎ ከጥናታቸው እዳይስተጓጎሉና ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ላይ አነስተኛ ውጤት እንዳያስመዘግቡ መምህራን የድጋፍ ትምህርት እየሰጡ እንዲቆዩና ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት እንዲልኩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከት/ቤቱ 7ኛB ክፍል፣ ከ1ኛ ደረጃ ተማሪዎችና ከሴት ተማሪዎች 1ኛ በመውጣት ሦስት ሽልማቶችን ያገኘችው ተማሪ ህይወት ስንታየሁ በርትታ በማጥናት ለውጤት መብቃቷን ተናግራ ሌሎች ተማሪዎችም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀምና በርትተው ማጥናት አለባቸው ብላለች፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ፣ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል፣ የኮሚዩኒቲ ት/ቤት ወላጅ-መምህር ኅብረት ሰብሳቢ አቶ ገዳሙ ጌታቸው፣ የት/ቤቱ ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች የታደሙ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ትምህርታዊ ጽሑፎች፣ ግጥሞችና ጭውውቶች በተማሪዎች ቀርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት