የዓሣን የፕሮቲን ይዘት ለማሳደግና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ከሚሠራው ‹‹ዓሢቱ›› ከተሰኘ ድርጅት ጋር ዩኒቨርሲቲው በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሐምሌ 18/2014 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ አብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ ዓሣን ከጫሞ ሐይቅ ብቻ ስለሚመገብ ምርቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴን ተጠቅሞ ምርቱን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ4 ዓመታት በፊት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማዕከል መሥርቶ የልኅቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተክሉ በዘርፉ ምርምሮችን ለማካሄድ ዩኒቨርሲቲው በዕቅድ ይዞ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በጋራ ለመሥራት የሚፈልግ ድርጅት መገኘቱ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የ‹‹ዓሢቱ›› መሥራች አቶ ዳግም ይትባረክ ድርጅታቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ የዓሣ ምርት መስጠት የሚያስችል አዲስ የዓሣ አመራረት ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አርባ ምንጭ ለዓሣ ምርት ምቹ ተፈጥሮ ያላት በመሆኗ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ዓሣን በብዛት ስለሚመገብ እንዲሁም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማዕከል ያለው በመሆኑ በጋራ ለመሥራት ተመራጭ ማድረጋቸውን አቶ ይትባረክ ጠቅሰዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ወደ ሥራ ገብተው ተሞክሮውን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ማድረስ ከተቻለ ኑሯቸውን ከማሻሻል ባለፈ የተሻለ የገበያ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ የተማሪዎችን ተረፈ ምግብ በማድረቅ ለዓሣዎች ምግብነት ማዋል ከቻለ ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚያስችለውም ጠቁመዋል፡፡

የድርጅቱ ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሴር ዶ/ር ኮሚኒስት ሲሳይ በበኩላቸው ድርጅቱ የዓሣ ምርትን በማምረት ለገበያ እስከ ማቅረብ ድረስ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ጠቅሰው አዲሱ ቴክኖሎጂ ብዙ ዕውቀትና ጉልበት የሚጠይቅ ባለመሆኑ ዓሣን በቀላሉ በማምረት የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል::

በስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የ‹‹ዓሢቱ›› እና የ‹‹Nuru International›› መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ፣ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፣ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማዕከል ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት