የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2014 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሐምሌ 18/2014 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት መንግሥት በመደበው በጀት የተሠሩ ሥራዎችና ውጤታቸውን እንዲሁም ያልተከናወኑ ተግባራትን በመለየት ምክንያታቸውን በጋራ ማየትና በቀጣይ ዓመት ዕቅድ ላይ እንዲካተቱ ማሻሻያ የሚደረግበት በመሆኑ ሪፖርቱን በጥንቃቄ ተገምግሟል፡፡ ከዚህም ባሻገር አፈጻጻሙ ከተገመገመ በኋላ ያልተፈጸሙ ተግባራት በየዘርፉ እስከ ግለሰብ ድረስ ትስስር እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዕቅድ ሲዘጋጅ የሚቆጠርና የሚለካ ሆኖ እንዲሁም ለአንድ ባለሙያ የሚሰጠው የሥራ አፈጻጸም ውጤት ከዩኒቨርሲቲው የአፈጻጸም ውጤት ጋር አብሮ የሚሄድ ሊሆን እንደሚገባውም ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መነሻነት በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲውን ስትራቴጂያዊ መሠረቶች እና መሠረታዊ መረጃዎች፣ የታቀዱ ዋና ዋና ስትራቴጂክ ጉዳዮች እና ተግባራት፣ የ2014 ዓ/ም በጀት አፈጻጸም፣ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም የመፍትሔ እርምጃዎች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በማካተት አቅርበዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት በመደበኛና በካፒታል በጀት ብር 3,478,841,245.00 ለዓመቱ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ተመድቦ 99.86 በመቶው ሥራ ላይ መዋሉን እንዲሁም የውስጥ ገቢን ከማሳደግ አንጻር ብር 66,403,541.57 መሰብሰብ መቻሉን አቶ አስፋው በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡

ከተግባራቱ መካከል የመምህራን የማዕረግ እድገትን አስመልክቶ በሙሉ ፕሮፌሰርነት 1፣ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት 6፣ በረዳት ፕሮፌሰርነት 22፣ 78 መምህራን በሌክቸረርነት እና 18 መምህራን በረዳት ሌክቸረርነት የማዕረግ እድገት ያገኙ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የመምህራን የትምህርት ዕድልን አስመልክቶ በሀገር ውስጥ 47 የ2ኛ ዲግሪ እና 14 የ3ኛ ዲግሪ እንዲሁም በውጪ ሀገር 2 የ2ና ዲግሪ እና 6 የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷል፡፡ መስከረም 29 እና 30/2014 ዓ/ም የተመረቁትን የ2013 ዓ/ም ተማራቂዎችንና ሐምሌ 25 እና 26/2014 ዓ/ም ያስመረቃቸውን ጨምሮ በቅድመ ምረቃ 8,185፣ በድኅረ ምረቃ 2ኛ ዲግሪ 1,047 እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ 14 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

2014 ዓ/ም 222 አዳዲስ ምርምሮች ጸድቀው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን ነባር ምርምሮች 639 በድምሩ 861 ምርምሮች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል 182ቱ ምርምሮች የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ የ‹‹Ethiopian Journal of Water Science and Technology (EJWST)›› ጆርናል እና ‹‹Ethiopian Journal of Business and Social Sciences›› ወቅቱን ጠብቀው ታትመው መሰራጨታቸው፣ 15 ትልልቅ የምርምር ፕሮጀክቶች (Grand Research Projects) መቀረጻቸው፣ በበጀት ዓመቱ ጥራትና የምርምር ሥነ ምግባርን የጠበቁ ምርምሮች እንዲካሄዱ ለ190 ተማሪዎች የምርምር ድጋፍ መደረጉ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተመለከተ የኢንዳክሽን ሞተር ኮንትሮል እና የእንቁላል መፈልፈያ ማሽኖች እንዲሸጋገሩ መደረጋቸው፣ 4 ቴክኖሎጂዎች፡- ሌዚንግ ማሽን፣ የሸንኮራ አገዳ ጁስ መጭመቂያ፣ የበቆሎ መፈልፈያና መልቲ ፐርፐዝ

መክተፊያ ሥራቸው ተጠናቆ ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ለመሸጋገር ዝግጁ መሆናቸው እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቴክኖሎጂ ፓኬጅ የ5 የፈጠራ ውጤቶች የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ማግኘቱ ከዘርፉ ዐበይት ክንውኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ በ3ኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በ2 ተከታታይ ዙሮች ለምግብነትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያገለግሉ ከ22,000 በላይ ችግኞች በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ግቢዎች እና በቤሬ ተፋሰስ መተከላቸው፣ በሻራ ቀበሌ አቡሎ ንዑስ መንደር የ3.5 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ ሥራ ተመርቆ ለአገልግሎት መዋሉ፣ በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ የሆነ ‹‹EASY WAYS to READ in ENGLISH” በሚል ርዕስ ከKG እስከ 4ኛ ክፍል ያለውን የክፍል ደረጃ መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፍኖተ ንባባ አጋዥ መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ መብቃቱ፣ በዞኑ ለሚገኙ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች 500 መጻሕፍት ድጋፍ መደረጉ፣ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው 10 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዝ በበጀት ዓመቱ ተቆራጭ መደረጉና የደም ልገሳም መካሄዱ፣ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች በአንድ ሚሊዮን ብር የምግብ እህል እንዲሁም በተመሳሳይ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ወገኖች 1.5 ሚልዮን ብር የሚያወጡ 700 የብርድ ልብሶች፣ 240 ጥንድ አንሶላዎችና 50 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት ድጋፍ መደረጉና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችንና የዘማች ቤተሰቦችን ለመደገፍ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችንና መምህራንን በማሳተፍ በተደረገው ሀገራዊ የድጋፍ ዘመቻ የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ት/ቤት 70,000 ሺ ብር እና አልባሳት መሰብሰቡ ከዋና ዋና የማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ለኦቾሎ ኦዶ፣ ቆላ ሻራና ጫሞ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ለአርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም ግምቱ 864,296.85 ብር የሆነ የግንባታ ዕቃዎች ወንበር፣ ጥቁር ሠሌዳ እና የማጣቀሻ መጻሕፍት መሰጠታቸው፣ ለሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል 114 ሺህ ብር የሚያወጡ የደም ናሙና መመርመሪያ እና የማዋለጃ አልጋ እንዲሁም ለ6,318 ሕፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች የነጻ ሕግ ድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱ፣ ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በትብብር በምዕራብ አባያ፣ ጨንቻ፤ አርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ገረሴ እና ቁጫ ወረዳዎች ለሚሠራው የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተደራሽ እንዲሆን ሙያዊና ቁሳዊ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑ፣ የእንሰት ቴክኖሎጂዎች ለ4 እንሰት አብቃይ ወረዳዎች ተደራሽ እንዲሆኑ 2.3 ሚሊየን ብር ተበጅቶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑ መልካም አፈጻጸም የተመዘገበባቸው ተግባራት መካከል መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ ከማስተዋወቅ አንጻርም በበጀት ዓመቱ 9 ፕሮግራሞች በዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት እና በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፣ 50 የቴሌቪዥንና 63 የሬዲዮ ዜናዎች በፌዴራልና በክልሉ ሚዲያ ተቋማት እንዲሁም 220 ዜናዎች በዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ተሠርተው በዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽና ፌስቡክ ገጾች፣ በዩኒቨርሲቲው ቴሌግራም እና ዩቲዩብ ቻናሎች በማስቀመጥ እንዲሁም በአዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጦች ላይ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ዜናዎችን 60 ጊዜ በማሳተም የዩኒቨርሲቲው ዓበይት ክንውኖች እንዲተዋወቁ ተደርጓል፡፡

ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ የሰርቪስ እና የመስክ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ማነስና አሮጌ መሆን፣ የተማሪዎች ምግብ ጥሬ ዕቃና የግብዓት አቅርቦት የገበያ ዋጋ ንረት፣ የግንባታዎች በወቅቱ አለመጠናቀቅ፣ ለሁሉም ካምፓሶች ለጥበቃና ደኅንነት ሥራ በቂ መሳሪያ አለመኖር ተጠቅሰዋል፡፡ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችን በተመለከተ ተሽከርካሪዎችን በማስጠገን እና በመከራየት ሥራዎችን ማከናወን፣ ከገበያ ዋጋ ንረት ጋር ላጋጠሙት ችግሮች የአንዳንድ ሥራዎችን መጠን በመቀነስና የበጀት ዝውውሮችን አስፈቅዶ መጠቀም መቻሉ ብሎም የግንባታ ተቋራጮች ሥራውን ሙሉ በሙሉ እንዳያቆሙ የሦስትዮሽ ስብሰባዎችን እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድና ከኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ጋር የምክክር ስብሰባዎች መካሄዳቸው ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እንዲሁም የአስተዳደር ዘርፍ ሥራዎች በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የመሥራት ደረጃን ማሻሻል፣ የምርምር ሥራ ውጤቶችንና የተላመዱና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ የማሸጋገር ሥራዎችን አጠናክሮ መሥራት፣ ከኦዲት ግኝት የፀዳ ተቋም መሆን፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችን ማበራከትና አሠራሮችን በማሻሻል ገቢን ማሳደግ፣ ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና አዲስ የተጀመሩት በብቃት እንዲሠሩ ትኩረት ሰጥቶ መደገፍ፣ መረጃን ማደራጀትና ለሚመለከታቸው ክፍሎች በጥራትና በተገቢው ጊዜ የማስተላለፍ ደረጃን ማሻሻል እንዲሁም የተጀመረውን የዩኒቨርሲቲውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ትኩረት የሚሹና በተጠናከረ ሁኔታ ሊሠሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን ጆርናሎችንና የትምህርት ፕሮግራሞች ዕውቅና ማሰጠት /Accreditation/፣ የ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት፣ የማስተማርና የማስመረቅ አፈጻጸም ደረጃን ማሻሻል፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የሳውላ ካምፓስ ወሰን ጉዳይን እልባት እንዲያገኝ ማድረግ እና የዩኒቨርሲቲውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ ማስጀመር ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ መሆኑን በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

በግምገማ መድረኩ ከካውንስል አባላት የአፈጻጸም ሪፖርቱን መሠረት ያደረጉና ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ አፈጻጸሞች ዙሪያ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት