የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ባቀረበው የዩኒቨርቲሲው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ሐምሌ 18/2014 ዓ/ም ግምገማዊ ውይይት ተካሂዶ ጸድቋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ የዩኒቨርሲቲውን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድና የ2014 ዓ/ም አፈፃፀምን መነሻ ያደረገና በተቀመጡ ግቦች ስር የተዘረዘሩ ተግባራት ሊለኩና ሊቆጠሩ በሚችሉ ሁኔታ የተዘጋጀ ነው፡፡ የበጀት ዓመቱ ዕቅድ ሲጸድቅ ከየዘርፉ ኃላፊዎች ጋር የዕቅድ ውል ስምምነት እንደሚካሄድ፣ የዘርፍ ኃላፊዎችም በኩላቸው ከስራቸው ካሉ ፈጻሚ ግለሰቦች ጋር ዕቅድን ቆጥሮ ወስዶ አፈጻጸምን ቆጥሮ በሚመለስበት አግባብ የውል ስምምነት በመፈራረም ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ተፈጻሚ እንደሚሆን እንዲሁም በየሩብ ዓመቱ በሚቀርበው የአፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ግብረ መልስ መሠረት ማሻሻያዎች እየተደረጉ እንደሚፈጸም ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡  

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሰሎሞን ይፍሩ ዩኒቨርሲቲው በ2015 በጀት ዓመት በመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ማኅበረሰብ ጉድኝት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ መሠረተ ልማትና አስተዳዳር ዘርፎች በስትራቴጂያዊ ግቦች በተደራጁ የውጤት አመልካቾችና ቁልፍ ተግባራት የተዘጋጀው ዕቅድ ለካውንስሉ አባላት ለግምግማ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ዕቅዱ ከካውንስል አባላት የሚሰጡ ገንቢ አስተያየቶችን በማካተት ለዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር ቀርቦ ሲጸድቅ ለሥራ ክፍሎች ይወርዳል ብለዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት በመማር ማስተማር ዘርፍ ለማከናወን ከታቀዱ ሥራዎች መካከል የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የመጀመሪያ፣ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞችን መከለስ፣ ለመምህራን ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ መስጠት፣ በሁሉም የትምህርት መስኮች የተማሪዎችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያበለጽጉ የትምህርት ይዘቶችን ማስፋፋት እንዲሁም ለትምህርት ፕሮግራሞች የተዘጋጁ ስታንዳርዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡

ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚሠሩ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ማጠናከር፣ አዳዲስና ነባር ምርምሮችን ማካሄድ፣ የተላመዱ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ለማኅበረሰቡ ማሸጋገር፣ ለዩኒቨርሲቲው አካባቢ ነዋሪዎችና ለሴቶች ነፃ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሥልጠና መስጠት፣ የSTEM ማዕከልና Mobile Lab ማቋቋም እንዲሁም የሻማና የሻራ የመጠጥ ውሃ፣ የዲንጋሞ አነስተኛ ኃይል ማመንጫ፣ የቲቲካ ወንዝ ድልድይና የጠዬ ወንዝ ድልድይ ፕሮጀክቶችን ማከናወን በምርምር፣ በማኅበረሰብ ጉድኝትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ከታቀዱ ተግባራት መካከል ናቸው፡፡

በተጨማሪም ለሴት ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በትምህርት የመዝለቅ አቅማቸውን ማሳደግ፣ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ማቋቋም፣ ተቋሙን የከፍተኛ ፍጥነት ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ማድረግ፣ በሁሉም ካምፓሶች የመንገድ መብራት ዝርጋታ ማካሄድ፣ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ለአስተዳደር ሠራተኞች በመጀመሪያ ዲግሪ 94፣ በ2ኛ ዲግሪ 15፣ በቴክኒክና ሙያ በተለያዩ ደረጃዎች 104 እና ለ50 የአስተዳዳር ሠራተኛ ቤተሰብ ነፃ የትምህርት ዕድል መስጠት በ2015 የበጀት ዓመት ለማከናወን ከታቀዱ ተግባራት መካከል ናቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት ጨምሮ ም/ፕሬዝደንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዳይሬክተሮች የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች ተሳትፋዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት