በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሚቲዎሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋከልቲ አዘጋጅነት ‹‹Potential Collaborations on Tropical Meteorology and Climate Research Some Ideas on Multi-Disciplinary Approach›› በሚል ርዕስ ሐምሌ 22/2014 ዓ/ም ሴሚናር ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሴሚናሩ በአሜሪካን ሀገር የሰሜን ካሮሊና የግብርናና ቴክኒካል ስቴት ዩኒቨርሲቲ/North Carolina Agricultural and Technical State University/ መምህርና ተመራማሪ ከሆኑት ፕ/ር አደመ መኮንን ጋር የተደረገ ሲሆን የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማማከር፣ የምርምር ንድፈ ሃሳቦችን በጋራ በመቅረጽና የገንዘብ ድጋፍ ማፈላለግ እንዲሁም የተለያዩ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ረገድ በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ፕ/ር አደመ መኮንን በመምህራንና ተማሪዎች ሥልጠና፣ በምርምርና ሌሎችም ዘርፎች በግላቸው ፋከልቲውን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን እንዲሁም የሚመሩትን ቡድንና ዩኒቨርሲቲያቸውን በማስተባበር አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ቀጣሪ ድርጅቶች ከተቀጣሪዎቻቸው ብዙ የሚጠብቁ መሆኑን የገለጹት ፕ/ር አደመ ተማሪዎች ከሚመረቁበት የትምህርት ዘርፍ ባሻገር ዓለም አቀፉ ገበያ በሚፈልገው ልክ መሠረታዊ የሒሳብ፣ የኮምፒውተር፣ የቋንቋና ሌሎችም ተጨማሪ ዕውቀትና ክሂሎቶች ሊኖሯቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የሚቲዎሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋከልቲ ዲን ዶ/ር ታደሰ ቱጁባ ፋከልቲው በ1 የመጀመሪያ፣ 3 የ2ኛና 3 የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቅሰው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራሞች አዲስ የተከፈቱ በመሆናቸው በዘርፉ የሠለጠኑ ሰዎችን በመጠቀም ፕሮግራሙን ለማሳካት አንዱ መንገድ በትብብር መሥራት ነው ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በምርምር ሥራቸው ዙሪያ ሃሳብና አስተያየት እንዲያገኙ በውይይቱ እንዲካፈሉ መደረጉን ዲኑ ገልጸዋል፡፡

የፋከልቲው መምህርና የዩኒቨርሲቲው የግራንትና ኮላቦሬቲቭ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ በበኩላቸው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ፕ/ር አደመ በራሳቸው ተነሳሽነት ከፋከልቲው ጋር በትብብር ለመሥራት መነሳሳታቸውን ተናግረው ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከእርሳቸውም ሆነ ከዩኒቨርሲቲያቸው ጋር የሚኖረው ግንኙነት መልካም ውጤት እንዲያመጣ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡

የሚቲዎሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋከልቲ ዲን አቶ ታደሰ ቱጁባን ጨምሮ የኢንስቲትዩቱ መምህራን እና የ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ሴሚናሩን ተካፍለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት