የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማ/ጉድ/ ዳይሬክቶሬት በጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ በሻማ ቀበሌ እያስገነባ የሚገኘውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የሥራ አፈፃፀም በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝደንት የተመራ የልዑካን ቡድን ጥቅምት 1/2015 ዓ/ም የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከዲዛይን እስከ ግንባታ ያለው ሂደት ሙሉ በሙሉ በዩኒቨርሲቲው ምሁራንና በማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት የሚመራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እስከ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገምና የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የመስክ ምልከታውን ማድረግ ማስፈለጉን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ በምልከታቸውም የፕሮጀክቱ የእስካሁን አፈፃፀም አበረታች መሆኑን መገንዘባቸውንና በሥራው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ባለሙያዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ በአካባቢው ያለውን አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ ተጽዕኖን  በመቋቋም  እያደረጉ የሚገኘውን አስተዋጽኦ ማድነቃቸውን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እንደ ዩኒቨርሲቲ መሰል ማኅበረሰብን ያሳተፉ ሥራዎችን በራስ አቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማከናወን ከፍተኛ ልምድ የተገኘበት መሆኑን የጠቀሱት ተ/ፕ በኃይሉ ፕሮጀክቱ እስከ ኅዳር አጋማሽ ድረስ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከኅብረተሰቡ የቀረበ ጥያቄን መሠረት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን የጥናትና ዲዛይን ሥራውን በማከናወንና የግንባታ ጨረታ በማውጣት ፕሮጀክቱን ለማሠራት ተሞክሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የጨረታ ሂደቱም በተለያዩ ምክንያቶች ሊሳካ ባለመቻሉ ከ3 ወራት በፊት በራስ አቅም ሥራውን ለማከናወን ተወስኖ ሥራው እንደተጀመረ ዶ/ር ተክሉ አውስተዋል፡፡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ለዘመናት ንጹህ ውሃ ሳያገኙ የቆዩ በርካታ የቀበሌውንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ የግብዓትና የባለሙያ ወጪዎች ሙሉ በሙሉ በዩኒቨርሲቲው የተሸፈኑ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ተክሉ የቀበሌው ማኅበረሰብ በአስቸጋሪው አከባቢያዊ ቁልቁለትና ዳገት ሳይበገር የግንባታ ዕቃዎችን በማጓጓዝና በሌሎች የግንበታ ሂደቶች ላይ በጉልበት እያደረገ ያለው አስተዋጽኦም ጉልህ ነው ብለዋል፡፡ ይህም የማኅበረሰብ  ጉድኝት ጽንሰ ሃሳብን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና መምህርና የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ኢ/ር ዘመድ መንበሩ ፕሮጀክቱ አንድ የምንጭ ማጎልበት ግንባታን፣  አንድ 25 ሺ ሊትር ውሃ መያዝ የሚችል የውሃ ማጠራቀሚያ (Reservoir) ግንባታን፣ የ6 ቦኖዎች ግንባታንና 6 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታን ያካተተ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ውሃውን በየመንደሩ ለማዳረስ የመሬት ስበትን/gravity) እንዲጠቀም ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝና በ3 ቦታዎች ላይም መቆጣጠሪያዎች (Water Break) እንደሚኖሩት ጠቁመዋል፡፡  የግንባታው ሂደት አሁን ላይ 68 በመቶ መድረሱን የገለጹት ተቆጣጣሪው በቀጣይ 1 ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ሥራው ሙለ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃልም ብለዋል፡፡

በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ተሻለ ደርቤ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በወረዳው በርካታ ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በሻማ ቀበሌ ዩኒቨርሲቲው እያሠራ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን የዘመናት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄ የሚመልስ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በወረዳው መንግሥትና ሕዝብ ስም ለዩኒቨርሲቲው ምስጋናቸውን  አቅርበዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም በውሃው ዘርፍም ሆነ በሌሎች መስኮች ማኅበረሰቡን ያሳተፉ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን ለማከናወን ወረዳቸው በትጋት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ላይ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች ጨምሮ፣ በሥራው የሚሳታፉ ባለሙያዎች፣ የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎችና የሻማ ቀበሌ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት