በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጁ ሰባት የፈተና መስጫ መዕከላት በሁለት ዙሮች ለማኅበራዊና ተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በሠላምና በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዩኒቨርሲቲው በሚገኙ ሁሉም ካምፓሶች በተዘጋጁ የፈተና መስጫ ማዕከላት ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት  2/2015 ዓ/ም የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሁም ከጥቅምት 8-11/2015 ዓ/ም የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን ፈተናው ከመሰጠቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ተፈታኞች መከተል ስላለባቸው የፈተና ሥነ-ምግባር፣ መብት፣ ግዴታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ገለፃ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ መስከረም 29/2015 ዓ/ም በበይነመረብ በተካሄደ መርሃ-ግብር ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድና የትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ፈታኝ መምህራን የተጣለባቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በፍጹም ኃላፊነት እንዲወጡ በአጽንኦት አሳስበው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች በሚገኙ የፈተና መስጫ ማዕከላት በሁለቱ ዙሮች ከደቡብ፣ ከኦሮሚያና ከሲዳማ ክልሎች የተወጣጡ ከ36 ሺህ በላይ ተፈታኞች ፈታናውን የተቀበሉ ሲሆን የፈተናው ሂደትም በስኬትና በሠላም መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡  ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ የምግብ፣ የመኝታና የሕክምና አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ ሲያቀርብ መቆየቱንም ዶ/ር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡ የፈተናው ሂደት ኩረጃና የፈተና ስርቆትን ያስቀረ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ዳምጠው ይህም ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ተለይተው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ ስለሚያደርግ  በዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋለውን የትምህርት ብክነት ይቀንሳል ብለዋል፡፡ ፈተናው በዚህ ደራጃ መሰጠቱ ከ1ኛ ደረጃ ጀምሮ ለሚገኘው የትምህርት ማኅበረሰብ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዳምጠው ከታች ካሉ የትምህርት ደረጃዎች ጀምሮ ተማሪዎችን በተገቢው ዕውቀት የማነጽና የኩረጃና የፈተና ስርቆት ዕድልን የመዝጋት ሥራ እንዲጀመር በር የከፈተ ነውም ብለዋል፡፡

የፈተናው ሂደት በስኬትና በሠላም እንዲጠናቀቅ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከፌዴራል ፈተናዎችና ምዘና አስተዳደር ጀምሮ ያሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን የገለጹት ዶ/ር ዳምጠው የክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ትምህርት መምሪያዎች፣ የወረዳ ት/ጽ/ቤቶች፣ የጋሞና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም የአርባ ምንጭና ሳውላ ከተሞች የጸጥታ መዋቅሮች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና አመራሮች እንዲሁም የፈተና ከሚቴዎች፣ የፈተና ማዕከል ኃላፊዎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ የጣቢያ አስተባበሪዎች፣ ፈታኞች፣  የምግብ ቤት፣ የክሊኒክ፣ የመኝታ ቤት፣ የጽዳት ወዘተ. ሠራተኞችና ባለሙያዎች ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በስኬት እንዲያጠናቅቅ የጎላ ሚና የተጫወቱ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ስም ፕሬዝደንቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ተማሪዎቹ ወደየመጡበት አካባቢ በሠላም መሸኘታቸውንም ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

ከተፈታኞች መካከል አስተያየቷን የሰጠችው ተማሪ ረሂማ መሐመድ ፈተናው በዚህ መልክ በዩኒቨርሲቲዎች በጥብቅ ቁጥጥር መሰጠቱ ኩረጃን በማስቀረት እያንዳንዱ ተማሪ የራሱን ብቻ እንዲሠራ ያስቻለ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ተማሪዋ ይህም በራሱ የሚተማመንና ከሌብነት የጸዳ ትውልድ ለማፍራት የሚያግዝ ነውም ብላለች፡፡ በዩኒቨርሲቲው የቀረቡ የምግብ፣ የመኝታና ሌሎች አገልግሎቶችም ምቹ እንደነበሩ የተናገረችው ተማሪዋ ሲወራ ከሰማችው በተግባር ያየችው አገልግሎት ተሽሎ መገኘቱንም ገልፃለች፡፡

ሌላኛው ተፈታኝ ተማሪ ዘሪሁን ካሳሁን በሰጠው አስተያየት ለፈተናው ጥሩ ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ ተናግሮ ፈተናውን ያለምንም ችግር በተረጋጋ ሁኔታ ተፈትኖ ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡ ፈተናው በጥብቅ ቁጥጥር የተሰጠ መሆኑን የተናገረው ተማሪው ይህም ከዚህ ቀደም ፈተና ወጣ ወይም ተሰረቀ የሚሉ አሉባልታዎችን ማስቀረቱንም ተናግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በነበረን የጥቂት ቀናት ቆይታም ከተለያዩ ቦታ ከመጡ ተፈታኞች ጋር በጥሩ ሁኔታ አሳልፈናል ብሏል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡት የ70 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ተፈታኝ አቶ ምህረቱ ቦንዱም በበኩላቸው ልጆቻቸውን ለማስተማርና በትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ ሊሆኑላቸው ባለመቻላቸው በተፈጠረባቸው ቁጭት ይህን ፈተና እንዲፈተኑ እንዳነሳሳቸው ጠቁመዋል፡፡ በ1977 ዓ/ም 11ኛ ክፍል እንደጨረሱ የሚገለጹት አቶ ምህረቱ ለፈተናው ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውንና በዩኒቨርሲቲው እስካሁን የነበራቸው ቆይታም መልካም እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በስኬት እንዲያጠናቅቅ የበኩላቸውን ለተወጡ ለፈታኝ መምህራን ጥቅምት 03 የአርባ ምንጭ አዞ እርባታ የመስክ ጉብኝትና የምስጋና እንዲሁም ጥቅምት 12/2015 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ ለፌዴራል ፖሊስ አባላትና አመራሮች የምስጋና መርሃ-ግብር በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ተካሂዷል፡፡


                                                                                                                                                                                                  የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት