ወ/ሮ ጥሩነሽ ግርማ መንገሻ ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘነበች ገለታ እና ከአባታቸው አቶ ግርማ መንገሻ በአርባ ምንጭ ከተማ የካቲት 21/1968 ዓ.ም ተወለዱ፡፡


ወ/ሮ ጥሩነሽ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ሰሜን ኦሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ፊት አውራሪ ኃይሌ ደጋጋ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ ጫሞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል፡፡


ወ/ሮ ጥሩነሽ ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሚያዝያ 10/2001 ዓ.ም በሂውማን ሪሶርስ ማኔጅመንት በደረጃ I፣ ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ2002 ዓ.ም በማርኬቲንግ /ሴልስማንሺፕ/ በደረጃ IV በዲፕሎማ ፕሮግራም እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሂውማን ሪሶርስ ማኔጅመንት ነሐሴ 25/2012 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡


ከኅዳር 1/1992 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 1992 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጽዳት ሠራተኛነት ለ6 ወራት በሙከራ ቅጥር፣ ከግንቦት 1/1992 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 30/ 1994 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ እንስቲትዩት በጥጉ.2 ቋሚ የጽዳት ሠራተኛ ሆነው  ተቀጥረዋል፡፡
ወ/ሮ ጥሩነሽ ከሐምሌ 01/1997 ዓ.ም ጀምሮ በደረጃ ጽሂ-3 በቤተ-መጽሐፍት ውስጥ በላይብረሪ አቴንዳንትነት፣ ከመስከረም 01/2001 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 01/2004 ዓ/ም ድረስ በደረጃ ጽሂ - 7 በቤተ መጽሐፍት መረጃ አገልግሎት ክፍል የሰርኩሌሽን ዴስክ ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል፡፡


ወ/ሮ ጥሩነሽ እስከ መስከረም 01/2006 ዓ/ም በነጭ ሣር ካምፓስ በቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት በሰርኩሌሽን ዴስክ በውሰት አገልግሎት ሠራተኛነት፣ ከመስከረም 02/2006 ዓ.ም ጀምሮ በዋናው ቤተ-መጽሐፍት በሰርኩሌሽን ትውስት ባለሙያነት፣ ከጥር 1/2006 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት ጽ/ቤት ስር በመፕ-8 ደረጃ መለስተኛ የፔሬዲካል አገልግሎት ባለሙያ፣ ከሰኔ 1/2007 ዓ.ም ጀምሮ በደረጃ መፕ-9 በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ሥራ ሂደት ስር መለስተኛ የቤተ-መጽሐፍት አኩዚሽንስ ባለሙያ፣ ከመጋቢት 14/2007 ዓ.ም ጀምሮ በጫሞ ካምፓስ ቤተ-መጽሐፍት በውሰት ክፍል ሠራተኛነት፣ ከመስከረም 01/2011 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሂሳብ ሠነድ ያዥ II ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡


ወ/ሮ ጥሩነሽ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች እናት ሲሆኑ ባደረባቸው ሕመም ሲረዱ ቆይተው ጥቅምት 13/2015 ዓ/ም በተወለዱ በ47 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በወ/ሮ ጥሩነሽ ግርማ ኅልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ ጓደኞችና የሥራ ባልደረቦች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

                                                                                                                                                                                                                               የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት