የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ በ2014 በጀት ዓመት ያካሄደውን የማዕድን ሀብት አለኝታ ጥናት ውጤት የክልሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ማዕድንና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን እንዲሁም የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት በወላይታ ሶዶ ጥቅምት 17/2014 ዓ.ም ይፋ አድርጓል። ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አፀደ አይዛ በ2014 በጀት ዓመት ያለፉ የጥናት ውጤቶችን መሠረት በማድረግ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ጥናቶች መደረጋቸውንና በርካታ የማዕድን ክምችት መኖሩን ማረጋገጥ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን አለኝታ በዓይነትና በመጠን በማስጠናትና የማዕድን ተፈጥሮ ሀብቱ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ እንዲኖረው ማድረግ  አንዱ የኤጀንሲው ተግባር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ኤጀንሲው ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕድን ሀብት አለኝታ ጥናት ለማድረግ 5 ትላልቅ ተቋማትን በማሳተፍ ባደረጋቸው ጥናቶች ውጤት ማግኘቱን ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ በኮንሶ ዞን በኮልሜ ክላስተር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጥናት እንደ ታንታለምና ኑቢየም የመሳሰሉ ብረት ነክ ማዕድናት እንዲሁም በቀጥታ ወደ ልማት ሊገቡ የሚችሉ እንደ ኢሜራልድ፣ አኮማሪን፣ አፓታይት ፣ አስቤስቶስና ፊልድስፓር  ማዕድናት  ክምችት ተገኝቷል፡፡

በተመሳሳይም በኮንሶ ዞን በላይቴ፣ በሰረቦ እና በአርበሌ ቀበሌያት በደለል ወርቅ መገኛ ቦታዎች በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት በተካሄደ ጥናት በተወሰኑ አካባቢዎች የደለል ወርቅ ስለመኖሩ በጥናቱ የተረጋገጠ ቢሆንም ግኝቱ ተጨማሪ ጥናት እንደሚጠይቅ ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡ በጊቤ ተፋሰስም በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ ጥናት ለሴራሚክ፣ ለሰልፈሪክ አሲድ እና ለውሃ ማጣሪያ የሚሆን የካኦሊን ማዕድን እንዲሁም በወላይታ ዞን በዱጉና ፋንጎ ወረዳ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት የኦፓል ክምችት ስለመኖሩ፣ በጋሞ ዞን በገረሴ ወረዳ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት የአጌት እና የአኮማሪን የኤክስፖርት ማዕድናት እንዲሁም ለሴራሚክና ለመስታወት ሥራ የሚውል የፊልድስፓር ማዕድን መኖራቸው መረጋገጡን ወ/ሮ አፀደ ተናግረዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳና በኮንሶ ዞን በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት በተካሄደ ጥናት ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚሆን የዶልማይት ማርብል፣ የኳርትዝ ፊልድስፓርና የግራናይት  ክምችት ስለመኖሩ፣ በጉራጌ ዞን በደቡብ ሶዶ ወረዳ በኬላ አካባቢ በኢትዮጵያ ማዕድንና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን  በተካሄደ ጥናት ለብረታ ብረት፣ ለወረቀትና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት ሊሆን የሚችል የላይም ስቶን (ኖራ) የማዕድን ክምችቶች መኖራቸውን ለማወቅ መቻሉን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸው በዚህም ላለፉት ዓመታት በክልሉ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ አሁንም በ2014 በተደረገው የጥናት ግኝት አበረታች ውጤት የታየበት በመሆኑ ተለይተው በወጡ አንዳንድ ማዕድናት ላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀትና ባለሀብቶችን በማስተሳሰር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ወ/ሮ አፀደ ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የማዕድን ሀብት አለኝታ ጥናት ውጤት ብዙ የተደከመበትና ከአውሬ ጋር በመጋፈጥና ሌሎች ውጣ ውረዶችን በማለፍ በከፍተኛ ልፋትና  ድካም በትኩረት ተሠርቶ የተገኘ ውጤት መሆኑን በመጥቀስ ለጥናት አቅራቢዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ኤጀንሲው ለሥራው መሳለጥ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ 6 ጥናቶች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ መካሄዳቸውንም ም/ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡  ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት የማዕድን ሀብቱን በዓይነትና በጥራት በመለየት እንዲለማ ማድረግና በተገኙ ግኝቶች ላይ የተደራጁ ወጣቶችንና አልሚ ባለሀብቶችን ወደ ሥራ ማስገባት  የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተ/ፕ በኃይሉ ጠቁመዋል።

የዩኒቨርሲቲው የኢንደስትሪ ትስስሪና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ሲያጠናቅቅ የቆየ ሲሆን በ2014 ዓ/ም ግን በልዩ ሁኔታ 12 ባለሙያዎችን በመመደብ ሁለት ፕሮጀክቶችን በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል ብለዋል፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ የዕውቀት ሽግግር ማድረጋቸውን የተናገሩት ዶ/ር ቶሌራ ዩኒቨርሲቲው ላበረከተው አስተዋጽኦ የተሰጠው የዕውቅና ምስክር ወረቀት እንደ ተቋም የበለጠ ሥራ ለመሥራት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረቡ ጥናት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ በሰጡት አስተያየት ሀገራችን በከርሰ ምድርና በገጸ ምድር ሀብቷ የበለጸገች መሆኗን የሚያሳዩ ውጤቶች ይፋ እየሆኑ በመምጣቱ መደሰታቸውን በመግለጽ በአሁኑ ሰዓት ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ ይሆናል ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እና ማጠቃለያ በሰጡበት ወቅት ሀገራችን ሉዓላዊነቷ የተደፈረው በኢኮኖሚ ባለማደጓ ምክንያት መሆኑን በመገንዘብ መንግሥት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት በትኩረት እየሠራ ስለሆነ የማዕድን ዘርፍም ኢኮኖሚው ላይ የሚጫወተው ሚና ከፍ እንዲል በሁሉም አካባቢዎች በልዩ ትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል። ሥራዎችን ተከፋፍሎ ወደ ተግባር ልንገባ ይገባል ያሉት ኃላፊው በዚህ ዓመት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት የዞንና የወረዳ አመራሮች ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡  

በጋሞ ዞን በገረሴ ወረዳና በኮንሶ ዞን በኮልሜ ክላስተር የተካሄደው የማዕድን ሀብት ጥናት ውጤት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በጊቤ ተፋሰስ የተካሄደው የማዕድን ሀብት ጥናት ውጤት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ በወላይታ ዞን በዱጉና ፋንጎ ወረዳ የተካሄደው የማዕድን ሀብት ጥናት ውጤት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ በደቡብ ኦሞ እና በኮንሶ ዞን የተካሄደው የማዕድን ሀብት ጥናት ውጤት በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት እና በጉራጌ ዞን በደቡብ ሶዶ ኬላ ወረዳ የተካሄደው የማዕድን ሀብት ጥናት ውጤት በኢትዮጵያ ማዕድንና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን ቀርቧል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት ለተከታታይ 5 ዓመታት በተለያዩ 6 ክላስተሮች ላይ የማዕድን ሀብት አለኝታ ጥናት በማድረግ ላበረከተው አስተዋጽኦ የመድረኩ ልዩ ተሸላሚ በመሆን የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል።

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት