በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና  ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማ/ጽ/ቤት በአርባ ምንጭ ከተማ እና አጎራባች ቀበሌያት በፈሳሽና ደረቅ ሳሙና አዘገጃጀት ሥራ ላይ ለተደራጁ 6 ማኅበራት ለሥራው የሚያግዙ የአላቂና ቋሚ ቁሳቁስ ድጋፍ ጥቅምት 17/2015 ዓ/ም አድርጓል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በኩል የሚሠሩ ሥራዎች በቁጥርም በዓይነትም እየሰፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  በአርባ ምንጭና በአካባቢው ለሚኖሩ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ ዙሮች በደረቅና ፈሳሽ ሳሙና ዝግጅት ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው ሥልጠና  የሰጠ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ተክሉ የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ማኅበራቱን ሥራ ከማስጀመርና ወደ ፊት ጠንክረው እንዲወጡ ከማስቻል አንፃር ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም የቁሳቁስ ድጋፉ በፈሳሽና ደረቅ ሳሙና ዝግጅት ላይ በዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ሥልጠና ወስደው ለተደራጁ 6 ማኅበራት  የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድጋፉ ሚክሰር፣ ሚዛን፣ የዓይንና የፊት መሸፈኛ፣ የፕላስቲክ በርሜል እና የተለያዩ ለሥራው የሚውሉ ኬሚካሎች የተካተቱበት ሲሆን አጠቃላይ የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ7 መቶ ሺህ ብር በላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ፍካት፣ ቆላ ሼሌ፣ ኤልጎ፣ ላንቴ፣ ልዩ መአዛና ሕብስት የሳሙና አምራች ማኅበራት ድጋፉ የተደረገላቸው ማኅበራት መሆናቸውንም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ ድጋፉ የተደረገላቸው ማኅበራት በሥልጠናው ያገኙትን የተግባር ዕውቀትና እንዲሁም አሁን ላይ የተደረገላቸውን ድጋፍ እንደ መነሻ በመጠቀም ጠንክረው በመሥራት ውጤታማ ለመሆን መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የጋሞ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራ ጥቃቅንና ማኒፋክቸሪንግ ዳይሬክቶሬት አስተባበሪ አቶ መሃሪ ካሳሁን እንደገለፁት ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ሥራ ፈላጊ ለሆኑ ወጣቶች በፈሳሽና ደረቅ ሳሙና አመራረት ዙሪያ ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል ያሉት አስተባባሪው ዩኒቨርሲቲው ለማኅበራቱ ያበረከተው የቁሳቁስ ድጋፍ ማኅበራቱን ከማጠናከር አንፃር ጉልህ ሚና ያበረክታል ብለዋል፡፡

የልዩ መአዛ ማኅበር አባል ወጣት ጸጋ በላይነህ በሰጠው አስተያየት ማኅበራቸው በአርባ ምንጭ ከተማ የተቋቋመ በፈሳሽና ደረቅ ሳሙና ምርት ላይ ለመሠማራት ጅምር ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በፈሳሽና ደረቅ ሳሙና አመራረት ሂደት ዙሪያ በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በዩኒቨርሲቲው የወሰዱ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተደረገላቸው ድጋፍ ማኅበሩን ሥራ ከማስጀመርና ወደ ፊት ውጤታማ በመሆን ሕይወታችንን ለመቀየር በእጅጉ የሚረዳ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ወጣት ጸጋ ዩኒቨርሲቲው ሥልጠና በመስጠትም ሆነ በቁሳቁስ ላደረገው ድጋፍ በማኅበሩ አባላት ስም ምስጋናውን  አቅርቧል፡፡

                                                                                                                                                                                                                                               የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት