ትምህርት ሚኒስቴር ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለተወጣጡ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተሮችና የሲስተም አስተዳደር ባለሙያዎች ‹‹Federated Identity System and Educational Roaming›› በሚል ርዕስ ከጥቅምት 24-26/2015 ዓ/ም  በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የትምህርት ሚኒስቴር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ተፈራ  የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ  የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ፣  የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አሠራር መቀየርና ለተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተናን መስጠትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተግባራት  እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ የሚጫወተው ሚና ጉልህ በመሆኑ የዘርፉን አሠራር ለማሻሻል ሚኒስቴሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን ይህም  ሥልጠና የዚሁ ሥራ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 የትምህርት ሚኒስቴር የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ዲጂታል ትምህርት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዘላለም አሰፋ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን ዓለም አቀፋዊ  ለማድረግና የተጠናከረ የእርስ በእርስ ትስስር ለመፍጠር በማዕከል ደረጃ ‹‹Education and Research Network›› የተሰኘ  ተቋም መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡  ሁሉም የምርምር ተቋማት ‹‹Educational  Roaming›› ሊኖራቸው ይገባል ያሉት ሥራ አስፈፃሚው በተቋማቱ የሚገኙ ተመራማሪዎችም ‹‹Identity Provider (IDP)›› መታወቂያን በመጠቀም መረጃን መለዋወጥና አብሮ መሥራት የሚችሉበት መንገድ ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ተመራማሪና አሠልጣኝ ዶ/ር ኩሪባቸው ግዛው በበኩላቸው ሥልጠናው በዋናነት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹Federated Identity System›› የተሰኘውን የመገናኛ መንገድ መጠቀም እንዲችሉ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሲስተሙ በዩኒቨርሲቲዎች ወጥ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት፣ የመማር ማስተማር እንዲሁም የተለያዩ ለምርምር የሚያግዙ መረጃዎችን ለማግኘት እርስ በእርስ መረጃ ለመለዋወጥ በእጅጉ የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተየየት የመማር ማስተማሩንና ምርምር ሥራን በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መደገፍ እንደ ሀገርም እንደ ተቋምም ያለው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ጠቁመው በሥልጠናው በተዳሰሱት አዳዲስ አሠራሮችና ሲስተሞች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በሥልጠናው አዳዲስ የተግባርና የጽንሰ ሃሳብ ዕውቀቶችን ማግኘታቸውን የገለጹት ሠልጣኞቹ ይህም ለቀጣይ ሥራችን በእጅጉ የሚጠቅም ነውም ብለዋል፡፡
በሥልጠናው መጨረሻም በሰው ሀብት አስተዳደር፣ ባለሙያ ቅጥር፣ ዲጂታል ፖሊሲ ማዕከል በማቋቋም፣ በዕቃ ግዥ ጥራትና የበይነ መረብ ሥልጠናንን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት