የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከ ̋UNHCR” ጋር በጋራ በመተባበር  ከጋሞ፣ ጎፋ እና ኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም ደራሼ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶችና ም/ፕሬዝደንቶች፣ ዳኞች፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ፣ አቃቢያን ሕጎች፣ የነጻ ሕግ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር  በነፃ የሕግ ድጋፍና በካምፓላ ስምምነት ዙሪያ ኅዳር 1/2015 ዓ/ም የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በኩል የነፃ ሕግ ድጋፍ ከ10 ዓመታት በላይ እየተሠጠ እንዳለና በአሁኑ ወቅትም በ  ̋UNHCR” የሚደገፍ  4 የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት  ለተፈናቃይ ወገኖች የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ በመሆኑም በምክክር መድረኩ በየማዕከላቱ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ያሉበትና የደረሱበት ደረጃ በመፈተሽና በቀጣይ ክፍተቶችን በመለየት የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲሰጥ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት መሆኑን ዲኑ ገልጸዋል፡፡  

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት ለአንድ ሀገር የተረጋጋ ሠላምና ኢኮኖሚ እድገት  ዜጎች በሠላም ወጥተው መግባት፣ በፈለጉት ቦታ ሀብት ንብረት ማፍራት መቻል፣ ተረጋግተው መኖር  መቻል እና የአዕምሯዊና አካላዊ ጤንነት መሟላታቸውንና መሳካታቸውን ለማረጋገጥ የፍትሕ ሥርዓቱ ወሳኝ ነው፡፡

ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት  በተለያዩ ምክንያቶች እየተፈጠሩ ያሉ የውስጥ መፈናቀሎችንና ከቦታ ቦታ ዝውውሮችን አስተናግዳለች ያሉት ተ/ፕ በኃይሉ እነዚህና መሠል ጉልህ ችግሮችን መፍትሄ እየሰጡ በስብዕና ላይ መሥራት እጅግ  አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የዘላቂ ልማት ግቦች ሁሉንም የሚያካትቱና እንደ አህጉር አቀፍም ኢትዮጵያ የምትገባቸው ስምምነቶች በመሆናቸው እነዚህን መነሻ በማድረግ የካምፓላ ስምምነት ውይይቱ አስፈላጊ ሆኗል፡፡

ተ/ፕ በኃይሉ በአሌና ደራሼ ልዩ ወረዳ፣ ኮንሶ ዞን የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ  መከፈቱ በጣም አስፈላጊ እንደነበር የገለጹት ተ/ፕ በኃይሉ ለፍትሕ ሥርዓቱ መገንባትና መሻሻል ለዜጎችም ሠላማዊና የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ እነዚህንና ሌሎች መሠል ሥራዎችን በጋራ በማቀድ ለተሻለ ስኬት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ት/ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ዳኛቸው ወርቁ በ2014 ዓ/ም የተከናወኑ የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት አገልግሎቶችንና ተግዳሮቶችን እንዲሁም በዘርፉ በያዝነው ዓመት ሊተገበሩ የታቀዱ ሥራዎችን አቅርበዋል፡፡ እንደ መ/ር ዳኛቸው ገለጻ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት መሠረታዊ ዓላማ የፍትሕ ተደራሽነትንና በእኩልነት ፍትሕ የማግኘት መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡ እየተሠራ ያለውን ሥራ መደገፍ፣ በኢኮኖሚ አቅም ምክንያት ከፍለው ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን ማስከበር ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የአገልገሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ፣ በሕግ ት/ቤት ውስጥ ተማሪዎች ከሚያገኙት የንድፈ-ሀሳብ ትምህርት ባሻገር በተግባር በአገልግሎቱ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የተሟላ ዕውቀት፣ ክሂሎትና አመለካከት ያላቸው የሕግ ምሩቃንን ማፍራት ነው፡፡

ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ 12 ማዕከላት ያሉት ሲሆን በጫሞ ካምፓስ የሕግ ት/ቤት ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ በአርባ ምንጭ ከተማ ፍርድ ቤት፣ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት፣ በከተማው ማረሚያ አስተዳደር፣ በጨንቻ፣ በብርብር (ምዕራብ ዓባያ)፣ በደራማሎ፣ በሳዉላ፣ ኮንሶ ካራት፣ ኮልሜ፣ ኦላንጎ እና  በጊዶሌ እንደሚገኙ ጠቁመው  የሕግ ምክር አገልግሎት፣ አቤቱታዎችን መፃፍ፣ ወክሎ መከራከር እና ማስታረቅ እንዲሁም ንቃተ-ሕግን ማስረጽ ከሚሰጡት የነፃ ሕግ ድጋፍ አገልግሎቶች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የካምፓላ ስምምነት መፈናቀልን መከላከል፣ ምላሽ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት የወጣ የመጀመሪያው አህጉራዊ ኮንቬንሽን ነው ያሉት ሌላኛው ሠነድ አቅራቢ የሕግ ት/ቤት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት አስተባባሪ መ/ር ሚካኤል መሠለ የካምፓላ ስምምነት፣ አንቀጽ 1 በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በትጥቅ ግጭቶች፣ በአጠቃላይ ሁከት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በአደጋ እና በልማት ፕሮጀክቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን መብቶች በግልፅ ይጠብቃል ብለዋል። አባል ሀገራት መፈናቀል በሚችሉ አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችንና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስልቶችን መዘርጋት፣ መተግበር፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና የሰው ልጅ አያያዝ እርምጃዎችን እና አስፈላጊ ከሆነም ለተፈናቀሉ ዜጎች አፋጣኝ ከለላ እርዳታ መስጠት አለባቸው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት መ/ር ሱራፌል ደመላሽ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የደረሱበትን ደረጃ በአኃዝ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ከተፈናቃዮቹም መካከል አብዛኛውን ቁጥር የያዙት ሴቶችና ሕጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አፈናቃይን ተጠያቂ ማድረግ መፈናቀል ዳግም እንዳይከሰት መፍትሄ ነው ያሉት የምክክር መድረኩ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ት/ቤቱ የተሠሩ ሥራዎችና ሊሠሩ የታሰቡ ጉዳዮች እንዲሁም የታዩ ክፍተቶችን በማንሳት ለመወያየት የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱ የማነቃቃት ስሜትና ሥራን በተነሳሽነት ለመሥራት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው የሕግ ት/ቤቱ እየሰጠ ያለው የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፈን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጠ ያለ መሆኑን በዝርዝር የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የሕግ ት/ቤት መ/ራን ምንም እንኳን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም 3ቱን ተልዕኮዎች በሚታይና በሚቆጠር አግባብ እየሠሩ፣ አቅም የሌላቸው ወገኖችን በመርዳት ስኬቶችን እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረው በቀጣይም ተነሳሽነታቸውን በማጠናከር የበለጠ እንዲሠሩና የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬቱም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ከጎናቸው እንደሚሆን በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ገልጸዋል፡፡

                                                                                                                                                                                         የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት