አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ላይ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሚውል 1.5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የብርድ ልብስና አንሶላ ድጋፍ ኅዳር 3/2015 ዓ/ም በመካላከያ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት አስረክቧል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ ::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ጦርነቱ ከተጀመረ ከጥቅምት 24/2013 ዓ/ም ጀምሮ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች በገንዘብና በዓይነት የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ በጀቱ በመቀነስ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሠራዊቱ ያበረከቱ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ዳምጠው በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት የነበረውን የወልዲያ ዩኒቨርሲቲን ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በተደረጉ የቁሳቁስ ድጋፎች ሥራ ማስጀመር ተችሏልም ብለዋል፡፡ የዛሬው ድጋፍም የሀገራቸውን ሠላምና ሉዓላዊነት ለማስከበር ሲሉ ጉዳት ደርሶባቸው በተለያዩ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የዩኒቨርሲቲዎች ማስተማሪያ ሆስፒታሎች በሕክምና ላይ ለሚገኙ የሠራዊቱ አባለት የሚውል ነውም ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው መሰል ሀገራዊ የትኩረት ሥራዎች መሥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያወሱት ፕሬዝደንቱ ለሀገራችን ሠላምና ልማት እውን መሆን ተቋሙና ማኅበረሰቡ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የግዥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብ/ጄኔራል ዓለምሰገድ ወንድወሰን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩን ሠላም፣ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር ሐሩር፣ ብርዱና የውሃ ጥም ሳይበግረው ውድ ሕይወቱንና አካሉን ሳይሰስት ለእናት ሀገሩ ለሚሰጠው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆን በገንዘብ፣ በምግብና በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም የደጀንነት ተግባሩን የበሰሉ ምግቦችን እስከ ምሽግ ድረስ በማቅረብ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም ለሠራዊቱ በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ያደረገ መሆኑን የተናገሩት ብ/ጄኔራሉ ዩኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት ያደረገው ድጋፍም ለሠራዊታችን ትልቅ የሞራል ስንቅ ነውም ብለዋል፡፡ ብ/ጄኔራሉ ለተደረገው ድጋፍም በሠራዊቱ ስም ልባዊ ምስጋናቸውን ለዩኒቨርሲቲው አቅርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ሀገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በከባድ ፈተና ውስጥ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ዩኒቨርሲቲው በገንዘብ፣ የደም ልገሳ በማድረግ፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች የቁሳቁስና የምግብ እህል ድጋፍ በማድረግ፣ በጦርነቱ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ከማቋቋም ረገድ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ የአሁኑ ድጋፍም የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሲሉ ቆስለው በሕክምና ለሚገኙ የሠራዊቱ አባላት የተደረገ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ድጋፉ 1000 ብርድ ልብስና 800 ጥንድ አንሶላ ያካተተና በገንዘብ ሲተመን 1.5 ሚሊየን ብር እንደሚያወጣ ገልጸዋል፡፡በቅርቡ ጦርነቱን ሠላምና በውይይት ለመፍታት በፌዴራል መንግሥትና በሕወኃት መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት በእጅጉ አስደሳች መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ተክሉ በቀጣይ እንደ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በሠላምና በመልሶ ግንባታ እንዲሁም በሰብዓዊ ድጋፍ ዘርፉ ዳይሬክቶሬቱ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በድጋፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉ/ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገራችን ሳትፈልግ የገባችበትን ጦርነት ለመቀልበስና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተደረገው ጥረት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ በጀቱ ላይ ካደረጋቸው ድጋፎች ባሻገር የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ጉልህ ሚና ሲጫወት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ወ/ሮ ታሪኳ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል በርካታ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች መከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ለሀገራቸው ሉዓላዊነትና ሠላም መከበር ትልቅና የማይተካ ዋጋ መክፈላቸው ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን የገለጹት ተ/ም/ፕሬዝደንቷ ከሰሞኑ በሕወኃትና በፌዴራል መንግሥት መካከል በዘላቂነት ግጭት ለማቆምና ችግሮችን በንግግር ለመፍታት በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሠላም ስምምነት እንደ ሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች በንግግር ለመፍታትና ፊታችንን ወደ ልማት እንድናዞር የሚያግዝ መሆኑን ተ/ም/ፕሬዝደንቷ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ እንደ ሀገር ለዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጥ የመንግሥት አቅጣጫ መሠረት በቀጣይ በሚኖሩ የሠላምና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ላይ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ተቋም የሚጠበቅብንን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት  እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዩኒቨርሲቲውና ማኅበረሰቡ ዝግጁ መሆኑን ወ/ሮ ታሪኳ ገልጸዋል፡፡


የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት