ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝደንትነት ውድድር ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም በወጣው ማስታወቂያ መሠረት የቀረቡ 13 ዕጩ ተወዳዳሪዎች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ፣ የመምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና የተማሪዎች ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው ሴኔትና ካውንስል አባላት፣ ነባር መምህራን እና ተመራማሪዎች በተገኙበት የስትራቴጅክ ዕቅዶቻቸውን ኅዳር 5/2015 ዓ.ም እያቀረቡ የሴኔት ድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራልና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትነት 13 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል፡፡ በመመሪያው መሠረት የስትራቴጅክ ዕቅድ ገለፃ በመገምገም በሴኔት አባላት ከ25% ነጥብ መሰጠቱን የገለጹት አቶ ፈጠነ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በቀጣይ 6 ዓመታት ዩኒቨርሲቲውን በሚመሩበት ወቅት ለዩኒቨርሲቲው ለውጥ የሚሠሩበትን ስትራቴጅክ ዕቅድ እያቀረቡ የሴኔት አባላትም በበኩላቸው የቀረበውን ገለጻ መሠረት በማድረግ ውጤት ሰጥተዋል ብለዋል፡፡

አቶ ፈጠነ አክለውም እንደተናገሩት በውድድሩ የትምህርት ዝግጅት ሁኔታ 30%፣ የሥራ ልምድ 25%፣ የስትራቴጂክ ዕቅድ ገለጻ ዝግጅትና አቀራረብ 25%  እና የዕጩ መልማይ ኮሚቴ ቃለ-መጠይቅ 20% ሆኖ ከ100% አጠቃላይ ውጤት ይጠቃለላል፡፡ እንደ አቶ ፈጠነ ዕጩዎች በሚያገኙት ከፍተኛ ውጤት መሠረት አስመራጭ ኮሚቴው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ያሉ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ለዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ የሚያሳውቅ ሲሆን ሥራ አመራር ቦርዱም በበኩሉ ከ100% ተጠቃሎ የተላከለትን የ5 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ውጤት ወደ 80% በመለወጥ የራሱን 20% ውጤት ሰጥቶ በሚገኘው ውጤት ስሌት መሠረት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉትን ዕጩዎች ለትምህርት ሚኒስቴር እንደሚያቀርብ  ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም በሚቀርበው መረጃ መሠረት ዩኒቨርሲቲውን የሚመራውን ፕሬዝደንት ይሾማል ሲሉ አቶ ፈጠነ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትን አወዳድሮ ለመመደብ ነሐሴ 16/2014 ዓ/ም የተመረጠው የሴኔት፣ የመምህራን፣ የተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ተወካዮችን ያካተተው አስመራጭ ኮሚቴ ከቦርዱ ተወካይ ጋር ግልፅና ተዓማኒነት በተሞላው መልኩ ውድድሩን በማከናወን ውጤቱን በየወቅቱ ለተሳታፊዎች ይፋ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በነገው ዕለትም የቃለ መጠይቅ ውጤት በማካተት ከ100% ውጤት በማጠናቀቅ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 5 ዕጩ ተወዳዳሪዎችን እንደሚለይ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት