በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም /GIS/  ሶሳይቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ኅዳር  3/2015 ዓ/ም ተከፍቷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ፎይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ካለው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ በመነሳት የጂ.አይ.ኤስ ቢሮ መከፈቱ  አንድምታው ብዙ እንደሆነና ለሌሎች በዙሪያ ላሉ ዩኒቨርሲቲዎችም አካቶ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው የያዘውን ዓላማ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመው ሥራዎቹንም ወደ መሬት ለማውረድ ቅርንጫፍ ቢሮው ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርና ተደራሽነትንም እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ እንደማኅበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብሎም ጂ.አይ.ኤስን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማምጣት ሁላችንም የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ማበርከትና በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅ የገለጹት ዶ/ር ሙሉጌታ ቢሮው እንዲከፈት ያላሰለሰ ጥረት ላደረጉት ሁሉ በኮሌጁ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ስለማኅበሩ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል የጂ.አይ.ኤስ እና ሪሞት ሴንሲንግ መ/ርና ተመራማሪ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሶሳይቲ  ሰብሳቢ ዶ/ር አስናቀ መኩሪያው እንደገለጹት የማኅበሩን መሠረታዊ ዓላማ የስነ-ምድር መረጃ መሰብሰቢያ፣ መተንተኛ እና ማሰራጫ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲታወቅና እንዲስፋፋ መርዳት፣ በኢትዮጵያ ለተሰማሩ የስነ-ምድር ባለሙያዎች ሙያቸውን በሚመለከት የጥናት፣  የመወያያ እና የትብብር መድረክ ማመቻቸት፣ በኢትዮጵያ የስነ-ምድር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርትና ምርምር እንዲስፋፋ ማገዝ እና የዘርፉን የፖሊሲ አቅጣጫዎች መጠቆም፣ የሙያውን ክብር ማስጠበቅ፣ ሙያተኞችን ማሰባሰብና  ጥቅሞቻቸውን በማስከበር የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ግዴታዎች እንዲወጡ መደገፍ ነው፡፡ በተጨማሪም በዘርፉ ለተሰማሩ መ/ቤቶች  ሙያዊ እገዛ ማድረግ፣ በሀገሪቱ የስነ-ምድር መረጃና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጥራት ላይ አስተዋጽዖ ማድረግ እንዲሁም  ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ብሔራዊና ዓለም-ዓቀፋዊ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር እና ትብብርን ማጠናከር ነው ሲሉ ዶ/ር አስናቀ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አስናቀ ገለጻ የማኅበሩ 2ኛ ቅርንጫፍ ቢሮ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመበት ምክንያት የኒቨርሲቲው ማዕከል በመሆኑና ዘርፉን ለማሳደግ ተነሳሽነት ስላለው እንዲሁም በደቡብ ቀጠና የተሻለ የሰው ሀብት በመኖሩና የሚሰጠውን ኃላፊነት ይወጣል ተብሎ በመታመኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሥርዓተ ትምህርት ላይ እንዲሁም ኮርስ ምደባ ላይ በመሳተፍ እና የመ/ራንን አቅም በማጎልበት የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ እና በደቡብ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን፡- የደቡብ ክላስተርን በማሰባሰብ ችግር ፈቺ ጥናቶችን ማጥናት፣ በሀገራችን ብሎም በዓለም አቀፍ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በጋራ መሥራት፣ ዩኒቨርሲቲው በሚኖረው ጆርናል ላይ ከአዲስ አበባ እና  ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ከጠቀሜታዎቹ መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ዶ/ር አስናቀ አክለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የም/ማ/ጉድኝት ም/ፕሬዝደት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደተናገሩት የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተምን በእያንዳንዱ ምርምሮቻችን ውስጥ ማካተታችን ለሀገር ልማትና ዕድገት የሚያመጣውን እሳቤ ተመራማሪዎች እንዲያስተውሉ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ማኅበሩ እንደ ሀገር ለሚያደርገው ጥረት ሙያውን ከማዳበር አንጻር በመማር ማስተማር፣ በመረጃ አቅርቦት እና በምርምር በማገዝ፣ ባለሙያዎችም ከማኅበሩ ጋር ያላቸውን ቁርኝት እና ትስስር በማጠናከር እንዲሁም የሚገኘውን ጥቅም ለማኅበሩ በመስጠት ቀጣይ ጊዜያቶችን በጋራ ለመሥራት የማኅበሩ ቢሮ በዩኒቨርሲቲው መከፈቱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ትብብሩንና ትስስሩን ወደፊት በማጠናከር ለሌሎች ምሳሌ በሚሆንበት አግባብ በቀጣይ እንደሚሠሩና ዩኒቨርሲቲው በሚያስተባብርባቸው አካባቢዎች በሙሉ ይህን ተልዕኮ የማሳካት ዕድል እንደሚኖር ተ/ፕ በኃይሉ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለጂኦግራፊ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ይህን መሰል ሕንጻ መድቦ መሥራቱ ለሌሎችም ጥሩ ተሞክሮ ነው ያሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ም/ ፕሬዝደንት እና የኢትዮጵያ ጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሶሳይቲ ም/ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ገደፋ የቅርንጫፉ መከፈት አሁን ላይ ገና ጅማሮ በመሆኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል የአባላቱን ከፍተኛ ጥረት ይሻል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በቀጣይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን፣ ወርክሾፖችን በማጠናከርና የተለያዩ ልምድ ልውውጦችን በማድረግ ያላግባብ ሙያው እንዳይባክንና መረጃ ያላግባብ እንዳይወሰድ የበኩላችንን ልናደርግ ይገባል ያሉት አቶ ብርሃኑ አባላቱ ስህተትን የሚያርሙ፣ የሚታዘዙና የሚተጉ ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሶሳይቲ የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ቢሮ ኃላፊ መ/ር ኃይለማርያም  አጥናፉ የ  ሥራዎች በጣም የተዘበራረቁና በዘፈቀደ የሚሰጡ በመሆናቸው ይሄንን ለማደራጀትና ለማስቀጠል የቢሮው መከፈት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ሀገራዊ ፕሮጀክቶችንና ጥናቶችን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከፌዴራል መንግሥት እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችና መምህራንራን እንዲሁም በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን አባል የማድረግና አጠቃላይ ማኅበሩን የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለባቸው መ/ር ኃይለማርያም ገልጸዋል፡፡

ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ቅርንጫፍ ቢሮው በዩኒቨርሲቲው መከፈቱ የተሻለ ነገር ለዩኒቨርሲቲው እንደሚያመጣና ለመማር ማስተማር ሂደቱም ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸው የሥራ ኃላፊነትን ለመውሰድ እንዲሁም የአፈጻጸም ሂደቱን ለመገምገም ያመች ዘንድ የጋራ ስምምነት እንዲኖርና ማኅበሩን የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንትን ጨምሮ የማኅበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ ዲን፣ የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል ኃላፊና መ/ራን፣ የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሶሳይቲ ቦርድ አባላት፣ የድኅረ-ምረቃ ት/ቤት እና የኢንደስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች እንዲሁም የኮሌጅ ም/ዲኖች በተገኙበት የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሶሳይቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡                                                                                                                    

                                                                                                                                                                                                                       የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት