ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርነት ውድድር ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም በወጣው ማስታወቃያ መሠረት የቀረቡ 7 ዕጩ ተወዳዳሪዎች የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባልና የኢትዮጵያ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና ም/ፕሬዝደንቶች፣ የሴኔት አባላት፣ የመምህራን ማኅበር ተወካይ፣ የተማሪ ኅብረት ተወካይና የአስተዳዳር ሠራተኞች ተወካይ በተገኙበት  የስትራቴጂክ ዕቅዶቻቸውን  ኅዳር 6/2015 ዓ.ም ካቀረቡ በኋላ የሴኔት ድምጽ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባልና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንታዊ ምርጫና በም/ፕሬዝደንት ማዕረግ የውሃ ቴክኖሎጂ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርነት ምርጫ  አስፈጻሚዎች ሰብሳቢ አቶ ፈጠነ ተሾመ ስለውሃ ቴክኖሎጂ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርነት ምርጫን አስመልክተው እንደገለጹት ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ለቀጣይ አራት ዓመታት ቢመረጡ ለመሥራት ያቀረቡት የዕቅድ ሃሳብ በዩኒቨርሲቲው ትልቅና እምቅ አቅም ያላቸው መምህራን እንዳሉ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ያቀረቡትን  ትልቅ ዕቅድ ወደ ተግባር የሚቀይር አሸናፊ ኢንስቲትዩቱን ወደፊት የሚያሻግርና የሚያስቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

አቶ ፈጠነ አክለውም የምርጫ ሂደቱ በጣም ፍትሐዊ፣ ግልጽ፣ ተዓማኒና የሁሉም ሰው ተሳትፎ የታከለበት ሲሆን በውድድሩ  የትምህርት ዝግጅት ሁኔታ 25%፣ የሥራ ልምድ 25%፣ ዋና ተግባርን ለማሳየት የሚቀርብ ዕቅድና ገለጻ 20%፣ የአመራርነት ክሂሎትና ብቃት ላይ የሚደረጉ ግምገማዎችና ቃለ መጠይቆች 15% እና ሴኔት የሚሰጠው ድምጽ  15% ሲሆን አብላጫውን ድምጽ የሚያስመዘግብ ተወዳዳሪ አሸናፊ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ውድድሩ በጣም ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ሲሆን በአጠቃላይ የቀረቡት የዩኒቨርሲቲው መ/ራን ነባር የሆኑ፣ መካከለኛ ደረጃ አገልግሎት ያላቸውና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ሁሉም 3ኛ ዲግሪ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይዘው የቀረቡት ስትራቴጂክ ዕቅዶች ከዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት  ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር  የሚገናኝ ሲሆን ሁሉም ባላቸው የይዘት አቀራረብ በሚያገኙት ነጥብ አሸናፊው እንደሚለይ ዶ/ር ዳምጠው ጠቁመዋል፡፡                                                                                                                            

                                                                                                                                                                                                                                                የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት