የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ጾታዊ ጥቃትንና ትንኮሳን መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ከዋናው ግቢና ከተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሴት ተማሪዎች ኅብረት አደረጃጀቶች ጋር ከኅዳር 30-ታኅሣሥ 01/2015 ዓ/ም በየካምፓሶቻቸው ውይይት አካሂዷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሰብአዊ መብት ምንነት፣ የሴቶች ሰብአዊ መብቶችና የሚፈጸምባቸው የኃይል ጥቃት፣ ከጾታዊ ጥቃት መገለጫዎች አንጻር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚታዩ የጾታዊ ጥቃት ዓይነቶችና መነሻቸው፣ የጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ መንስዔዎችና መከላከል የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች ውይይቱ ካተኮረባቸው ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ በኢትዮጵያ ለ17ኛ ጊዜ ከተከበረው የ2015 ዓ/ም የነጭ ሪባን ቀን ጋር ተያይዞ የውይይት መድረኩ መመቻቸቱን የተናገሩት በዳይሬክቶሬቱ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ በተቋሙ ሴት ተማሪዎች በተለይ ከውጤት ጋር በተገናኘ በመምህራንና በሌሎች አካላት የሚደርስባቸውን ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት ለመከላከል እና ሃሳባቸውን ነጻ በሆነ መንገድ እንዲገልጹ ለማስቻል ከሴት አደረጃጀቶች ጋር የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ ከዚህ ቀደም ከሴት ተማሪዎች ኅብረት አደረጃጀቶች ጋር በየጊዜው የሚያደርገው ውይይት በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን የገለጹት ቡድን መሪው የግንዛቤ ክፍተቶችን ለመሙላት ውይይቱ የጎላ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በተቋሙ ሴት ተማሪዎች ሰላማዊና ነጻ በሆነ መንገድ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ቀጣይ የጋራ ሥራዎችን አስመልክቶ በእለቱ መነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ጥናቶችን መሠረት ያደረጉ በዩኒቨርሲቲዎች ለሴት ተማሪዎች የሚሰጡ ቅድሚያ ግምቶችና አድሏዊ አስተሳሰቦች በሰነዱ ተካተዋል፡፡ በዚህም 8.2 በመቶ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የአድሏዊ አስተሳሰቦች ተጠቂ እንደሆኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተጠቅሷል፡፡

በውይይቱ የዋናው ግቢና የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሴት ተማሪዎች ፕሬዝደንቶችና የሴት ተማሪዎች ኅብረት አደረጃጀት አባላት ተገኝተዋል፡፡


የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት