ዓለም አቀፍ የነጭ ሪባን ቀን ‹‹ሴቷን አከብራለሁ! ጥቃቷንም እከላከላለሁ!›› በሚል መሪ ቃል ታኅሣሥ 7/2015 ዓ/ም በሳውላ ካምፓስ ተከብሯል፡፡ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ በሀገራች ለ17ኛ ጊዜ ሲከበር ቆይቷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹የነጭ ሪባን ቀንን ማክበር ከተጀመረ ረዥም ጊዜ የቆየ ቢሆንም የተጠበቀውን ያህል ለውጥ እየመጣ አይደለም›› ያሉት የሳውላ ካምፓስ አስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተርና የሳውላ ካምፓስ ዲን ተወካይ አቶ ዘለቀ ዶሳ በዓሉን ከማክበር ባለፈ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ያገኘነውን ግንዛቤ ወደ አካባቢያችን በመውሰድ ማኅበረሰቡን ልናስተምርበትና ወደ ተግባር ልንቀይረው ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመቀየር ችግሮች እንዳይፈጠሩ መከላከል፣ ከተፈጠሩም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ችግሮቹን ለመፍታት እንዲሁም ሕግ ተላላፊዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሊሆን እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ የነጭ ሪባን ቀን ወንዶች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል አጋርነታቸውን የሚገልጹበት ቀን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር ወንዶች ነጭ ሪባን በደረታቸው በማድረግ የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ሂደት ውስጥ አጋርነታቸውን የሚያሳዩበት ብሎም በሴቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ እንዲሁም ጥቃት ሲደርስባቸው ዳር ቆሞ ላለመመልከት ቃል የሚገቡበት ነውም ብለዋል፡፡

ሰብአዊ መብቶች ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጾታ፣ ዕድሜ ሳይለዩ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ በእኩልነት የሚከበሩለት መብቶች ናቸው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት መምህር አቶ አብርሃም ክንፈ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙ ባህላዊና ልማዳዊ አስተሳሰቦች ተገዢ በሆኑ አንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ሴቶችን ዝቅ አድርጎ መመልከትና እንደ መጠቀሚያ መቁጠር መጠኑ ቢለያይም ዛሬም የሚስተዋል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ስነ ልቦናዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋልም ብለዋል።

አክለውም የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር የሴቶችን የእኩልነት መብት መሠረታዊ መብት በማድረግ ያካተተ ሰነድ ሲሆን የሴቶች የእኩልነት መብት ሳይከበር የሴቶችን መብት እና የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ የማይቻል መሆኑን እንደሚያመላክት መ/ር አብርሃም ገልጸዋል፡፡በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ ሰዎች ሁሉ የማይገረሰስ እኩል መብት እና ክብር ያላቸው ስለመሆኑና ይህም ለዓለም ሰላም መከበር እና ለሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች መረጋገጥ ድርሻ እንዳለው መደንገጉን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ጾታዊ ትንኮሳንና ያልተገባ ባሕርይን ለማስወገድ የወጣ ደንብ መኖሩንም መ/ር አብርሃም ጠቁመዋል፡፡

የሴቶችን ጥቃትና ትንኮሳ ለመከላከል ዳይሬክቶሬቱ የሚሠራቸውን ዋና ዋና ሥራዎች በዝርዝር ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ የነጭ ሪባን ቀንን ማክበርን ጨምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመጡ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ ፕሮግራም እንደሚያዘጋጅ እንዲሁም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የሕይወት ክሂሎት፣ ስነ-ተዋልዶ ጤና፣ ሥርዓተ ጾታና ጾታዊ ትንኮሳን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ለተማሪዎችና ሠራተኞች ጥቃትን የመከላከል እንዲሁም ጥቃት ደርሶባቸው አቤቱታ ይዘው ለሚመጡ ሴቶች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ዳይሬክቶሬቱ የበኩሉን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንዳለ አቶ ዛፉ አክለዋል፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በተወሰነ አካል ብቻ የሚፈቱ ሳይሆን ሁሉም በባለቤትነት ትኩረት ሰጥቶ ሊከላከልና ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡ በሥርዓተ ጾታ ላይ ያለውን አመለካከት ለመቀየር በተደጋጋሚ ሥልጠናዎች ሊሰጡ እንደሚገባም አክለዋል፡፡ በመጨረሻም ከጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት ጋር ተያይዞ በአካባቢው እየተከሰቱ ያሉ ጉዳዮችና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጫናዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ለቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡  

                                                                                                                                                                                      የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት