የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በከተማው ከሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች በአዲሱ የኤች አይ ቪ/HIV/ ፈጣን ምርመራ አልጎሪዝም ዙሪያ ከመጋቢት 16-18/2015 ዓ/ም ድረስ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፈለቀ ገ/መስቀል እንደገለጹት ሥልጠናው ባለሙያዎች አዲሱን የምርምራ አካሄድና አሠራር እንዲገነዘቡ ከማድረጉም ባሻገር በዘርፉ የሚከናወኑ የምርመራ ሥራዎችን ከዘመኑ ጋር አብረው የሚሄዱና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል፡፡ በሕክምናና ጤና ዘርፍ ያሉ አሠራሮች ምርምርንና የተለያዩ የውጤታማነት ፍተሻዎችን መሠረት አድርገው በየጊዜው የሚቀየሩና ለውጦች የሚደረግባቸው በመሆኑ ኮሌጁ በተለያዩ ጊዜያት የጤናና ሕክምና ባለሙያዎችን ከመስኩ አዳዲስ ግኝቶችና አሠራሮች ጋር የሚያስተዋውቁና ሙያን የሚያሻሽሉ እንዲሁም በወባ በሽታ ምርመራ፣ ሕክምና አሰጣጥ፣ ቁጥጥርና መከላከል አዳዲስ አሠራሮች ዙሪያ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ማዕከሉ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ መሰል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎችን የመስጠት ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳዴማ ሻንቆ በበኩላቸው  ጽ/ቤቱ ከኮሌጁ የሙያ ማሻሻያ ማዕከል ጋር የጤና ባለሙያዎችን አቅምና ሙያ ከማሻሻል አንጻር በትብብር እየሠራ መሆኑን ገልጸው በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጡ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎችም የባለሙያዎችን ዕውቀት ከማዳበር፣ ወቅታዊ ከማድረግ እና ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሻሻል ብሎም የተገልጋይ እርካታን ከፍ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የሚሰጣቸው የምስክር ወረቀትም ለሙያ ፍቃድ ዕድሳትና ለደረጃ ዕድገት በእጅጉ ይጠቅማቸዋልም ብለዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተጀመረው የትብብር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያወሱት አቶ ሳዴማ ዩኒቨርሲቲው የመስኩ ባለሙያዎችን አቅም በመገንባትና ሙያዊ ድጋፎችን በማድረግ የከተማውን የጤና ዘርፍ እየደገፈ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኅብረተሰብ ጤና ላቦራቶሪ አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ የመጡት አቶ ዘሪሁን ዘውዴ በሰጡት ሥልጠና በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ ያሉ ፈጣን የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ኪቶች በተለያዩ አህጉራት፣ ሀገራትና አካባቢዎች ሊኖሩ የሚችሉትን የቫይረሱን ዝርያዎች በእኩል ደረጃ የማግኘት አቅማቸው ውስንነት እንዳለው አመላክተዋል፡፡  በመሆኑም የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ያለውን ውስንነት ከግምት በማስገባት በኪቶቹ የሚከናወኑ ምርመራዎች በቁጥር ከሦስት በማያንሱ የተለያዩ ኪቶች አልጎሪዝም ጥምረት  መከናወን እንዳለባቸውና በአልጎሪዝሙ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ኪቶችም በሀገር ውስጥ ጥናት ተፈትሸውና ተገምግመው ቫይረሱ ያለባቸውን ከሌለባቸው በእርግጠኝነት የመለየት አቅማቸው እንዲሁም በተጨባጭ ከሀገራዊ የምርመራ አገልግሎት አሰጣጥ ስርጭት አንጻር ተስማሚ የአጠቃቀም ባህርያት እንዳሏቸው ማረጋገጥ እንደሚገባ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡  

በዚህም መነሻነት ሀገራት የሚጠቀሟቸውን የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ፈጣን ኪቶች አልጎሪዝም ጥምረት ከ3-5 ዓመታት ባለ ጊዜ ውስጥ ውጤታማነታቸው ከተለያዩ መስፈርቶች አንጻር ተገምግሞ ሊቀየሩ እንደሚችሉም አቶ ዘሪሁን አክለው ገልፀዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው አዲስ ከተቀየረው የኤች አይ ቪ. መመርመሪያ ፈጣን ኪቶች አልጎሪዝም አሠራርና አተገባበር ጋር እንዲተዋወቁ ያደረጋቸው መሆኑን ተናግረው በቀጣይም መሰል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች ቢሰጡ ባለሙያው ከወቅታዊ የሳይንስ ግኝቶችና ከመስኩ አዳዲስ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አሠራሮች ጋር  እንዲተዋወቅ ከማድረግ አንፃር የማይተካ ሚና እንዳላቸውና ይህም ለመስኩ ሥራ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተመተባበር ሥልጠናውን እንዲያገኙ በማድረጉ አመስግነዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት