የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል ጋር በመተባበር መጋቢት 19/2015 ዓ/ም ‹‹የኢንተርኔት መገደብ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?›› በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ በተማሪዎች መካከል የክርክር መድረክ አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ መሰል የክርክር መድረኮችን በማዘጋጀት ተማሪዎች በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን በተግባር እንዲለማመዱና ለሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ ማመቻቸት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡  ዶ/ር ዓለማየሁ አክለውም ወጣቶች ምክንያታዊ እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነትና ነፃነት ተሟጋች በመሆን ከቀደምት አባቶች በአደራ የተረከብናትን ሀገር በታማኝነት በመጠበቅ ለሀገራቸውና ለአካባቢያቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ እንየው ደረሰ እንደገለጹት የክርክር መድረኩ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በሰብአዊ መብትና በሕገ መንግሥት ዙሪያ የሚማሩትን ትምህርት ወደ ሥራው ዓለም ሲገቡ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚያጋጥሟቸውን ጉዳዮች አስቀድመው በተግባር ልምምድ በማድረግ የመናገር፣ የመከራከርና የማሳመን ብቃታቸው እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡ አቶ እንየው በቀጣይም የአምሳለ ፍርድ ቤትና ሌሎች መሰል የክርክር መድረኮችን ሀገራችን ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸውና ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችና በሕገ-መንግሥቱ ላይ በማዘጋጀት ተማሪዎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ሀሳባቸውን በተገቢው መንገድ መግለጽና መሟገት እንዲሁም ማሳመን የሚያስችል ልምድ ይዘው እንዲወጡ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማእከል ሲኒየር አድቮኬሲና ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር ቃልኪዳን ተስፋዬ በበኩላቸው  ማእከሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን አቅም የማጎልበት፣ ጥበቃዎችን የመስጠትና ሌሎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ኦፊሰሯ በማእከሉ በተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ክለብ ወጣቶች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሆኑና ከአልባሌ ድርጊቶችና ግጭቶች በመራቅ የአካባቢያቸውን ብሎም የማኅበረሰቡን ሰላም እንዲጠብቁ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ መሰል የተማሪዎች ክርክሮችም ተማሪዎች የመናገርና የመግለጽ ክሂሎታቸውን እንዲያጎለብቱ፣ ሰብአዊ መብቶችን የሚመለከቱ ችግሮችን እንዲለዩና በችግሮቹ ላይ በመወያየት የራሳቸውን መፍትሔ ማምጣት እንዲችሉ የሚያበረታታ መሆኑን ኦፊሰሯዋ ገልጸዋል፡፡

‹‹የኢንተርኔት መዘጋት ተገቢ ነው›› በሚል ርእስ  ክርክር ያቀረበችው የሕግ ት/ቤት የ4ኛ ዓመት ተማሪ መቅደላይት ፈቃደ እንደ ሀገር በነበረው የውጥረት ጊዜ የሐሰት ፕሮፖጋንዳዎች በየቦታውና በየአቅጣጫው እየተነዙ ሀገራችን ሁኔታውን መቆጣጠር እስከሚያቅታት ድረስ  ግጭቶች መፈጠራቸውን እንዲሁም ሀገር በተለያዩ ውጥረቶች ውስጥ በገባችበት ወቅት ኅብረተሰቡ በቂ የሆነ የኢንተርኔት አጠቃቀም ግንዛቤ ስላልነበረው ነገሮችን ከነበሩበት ይበልጥ እንዲባባሱና እንዲስፋፉ በማድረግ የተለያዩ ጉዳቶች መድረሳቸውን አንስታለች፡፡ እንደ ተማሪ መቅደላይት ገለጻ ለችግሮች መባባስ ዋነኛው ምክንያት ኢንተርኔት በመሆኑ ኢንተርኔት ለአላስፈላጊ ተግባራት፡- ግጭት ለመቀስቀስ፣ ሕዝብን ለማሸበር፣ ሀገርን ለመጉዳት አገልግሎት ላይ የሚውል ከሆነ መንግሥት የኢንተርኔት አማራጮችንና የሰዎችን የመናገር መብትም ጭምር መገደብ እንዳለበት በሕገ-መንግሥቱ ላይ በግልጽ መቀመጡን በክርክሯ ጠቁማለች፡፡ ተማሪ መቅደላይት በክርክሩ በተሻለ ሁኔታ ሀሳቧን በመግለጽ የዕለቱ ምርጥ ተከራካሪ ሆና ተመርጣለች፡፡

የ3ኛ ዓመት የሕግ ተማሪ የሆነችውና ሌላኛዋ የዕለቱ ተከራካሪ ተማሪ ሠላማዊት መላኩ ባቀረበችው የመከራከሪያ ሃሳብ የኢንተርኔት መዘጋት ወይም መገደብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 የተደነገገውን የሰውን ልጅ የመናገርና ሃሳቡን የመግለጽ መብት እንደሚያሳጣ ገልጻለች፡፡ መንግሥት እያደረገ ያለው የኢንተርኔት ማቋረጥ ሕጎችን ባለመከተሉ የሥራ መስተጓጎልና  ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት እየተጋፋ ነውም ብላለች፡፡

በመጨረሻም በክርክሩ 1ኛ ለወጡ ሁለት ተከራካሪዎች ለእያንዳንዳቸው ብር 2,500 እና 2ኛ ለወጡ ሁለት ተከራካሪዎች ለእያንዳንዳቸው ብር 2,000 ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን የዕለቱ ምርጥ ተከራካሪ የነበረችው ተማሪ መቅደላይት የ1,000 ብር ተጨማሪ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት