የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመሥራት መጋቢት 19/2015 ዓ/ም ትውውቅ አድርጓል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በትውውቅ መርሃ ግብሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ገጽታና ተግባራት በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንዲሁም የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮግራም ሥራዎች በፕሮግራም ማኔጀሩ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ቀርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው የውኃ ምኅንድስናና የምኅንድስና ተቋም በመሆኑ ከተለያዩ ሴክተሮች ጋር በቅንጅት መሥራቱ ለሀገር ልማት ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሎጀስቲክ ኃላፊና የባሕር ኃይል አዛዥ ተወካይ ኮሞዶር ዋላፃ ዋቻ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውኃ መስክ የረዥም ዓመታት ልምድና ተሞክሮ ያለው መሆኑን አስታውሰው ባለው የተደራጀ አቅምና የተማረ የሰው ኃይል በየትኛውም ሴክተር ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት ተቋም ነው ብለዋል፡፡ በሀገራችን ለዘመኑ የሚመጥን የሀገር መከላከያ ኃይል በማደራጀት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ በፊት ከነበረው የምድርና የአየር ኃይል ባሻገር የባሕር ኃይል መደራጀቱንና በሀገራችን ባሉ ውኃማ አካላት ላይ ግዳጆችን ለመወጣት የሰው ኃይል ከማሠልጠን ጋር ተያይዞ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ኮሞዶር ዋላፃ ገልጸዋል፡

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ም/አዛዥና የትምህርትና ሥልጠና ተወካይ ኮማንደር ከበደ ሚካኤል በበኩላቸው ባሕር ኃይል ብሔራዊና ሀገራዊ አቅምን የበለጠ ለማሳደግ በሚያከናውናቸው ተግባራት አጠቃላይ የውስጥ ውኃማ አካላትን ይዘት፣ ጥልቀት፣ ስፋትና ጠባይ ለማጥናት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዕውቀት ማገዙን ገልጸው በቀጣይም የሁለትዮሽ ትብብር ሰነድ ተዘጋጅቶ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት