የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት በሀገር አቀፍ አምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር አሸንፈው ለተመለሱ የት/ቤቱ ተማሪዎች ግንቦት 24/2015 ዓ/ም አቀባበል አድርጓል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተማሪዎቹ ያመጡት ውጤት የት/ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች የጋራ ሥራ ውጤት መሆኑን ገልጸው የተገኘው ውጤት ተማሪቹን በተለያዩ መድረኮች ተፈላጊ የሚያደርግ፣ ለመውጫ ፈተና በራስ የመተማመን አቅማቸውን የሚያሳድግና የትምህርት ጥራት እድገትን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ ገለጻ መንግሥት ሴት ተማሪዎች ከወንዶች አቻዎቻቸው እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እየሠራ ባለበት ሁኔታ ሁሉም የት/ቤቱ ተወዳዳሪዎች ሴት ተማሪዎች መሆናቸውና አቻ ወንዶችንና ሴቶችን አሸንፈው ለዚህ ድል መብቃታቸው ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ት/ቤቱ ከመማር ማስተማር ባሻገር በርካታ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን በመሥራት ጎልቶ የወጣ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ጠቅሰዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ት/ቤቱ በስኬቱ ለሌሎች አርአያ መሆኑን ተናግረው በውድድሩ የኢትዮጵያ ሕግ ት/ቤቶችን በማሸነፍ በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው በአምሳለ ፍርድ ቤት የመሳተፍ ዕድል መገኘቱ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡
የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት እንደ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም ት/ክፍሎች ተወዳዳሪ መሆኑ የዩኒቨርሲቲውን ደረጃ ከፍ ያደርጋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቷ የተገኘው ውጤት ፋይዳው የጎላና በተለይ ሴት ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት መሆኑ እጅግ አበረታች፣ አነቃቂና አስደሳች የሚያደርገው በመሆኑ መምህራን ጥረታቸውን ቀጣይ እንዲያደርጉ አሳስበው ለተወዳዳሪዎቹ በቀጣይ ውድድርም መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ የት/ቤቱ ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸው ለመጀመሪያ ጊዜ 2014 ዓ/ም 2ኛ በመውጣትና ምርጥ ጽሑፍ በማቅረብ ዋንጫ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዲኑ ገለጻ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ አምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር 21 ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በግማሽ ፍጻሜ ውድድር የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን እንዲሁም በፍጻሜ ውድድሩ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲን በማሸነፍ የዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ በቀጣይ ኅዳር ወር/2016 ዓ/ም ተወዳዳሪዎቹ በአፍሪካ መድረክ በአምሳለ ፍርድ ቤት ኢትዮጵያን ወክለው በታንዛንያ አሩሻ ላይ በሚካሄደው ውድድር የሚሳተፉ መሆኑን ጠቁመው ይህ ስኬት እውን እንዲሆን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር፣ ሕግ ት/ቤትና መምህራን ትልቅ ድጋፍና አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት መምህርና የውድድሩ አስተባባሪ መ/ር እምሻው ተሾመ በበኩላቸው ውድድሩ አድካሚና ልምድ ያላቸው አካዳሚክ ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮችና የውጭ ዜጎች የተሳተፉበትና አምስት ዳኞች የዳኙበት ትልቅ ውድድር መሆኑን ገልጸው የሁሉም የሥራ ክፍሎች ድጋፍ ውጤት በሆነው ሽልማት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት 4ኛ ዓመት ተማሪና ተወዳዳሪ መቅደላይት ፈቃደ ውድድሩ ፈታኝና ጠንካራ እንደነበር አስታውሳ በዕውቀት በታነጹ መምህራን ድጋፍ ማሸነፍ ችለናል ብላለች፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ በሀገራዊ አምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር ተሳትፈው ድል ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ለእያንዳንዳቸው የ3,000.00 ብር የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት