የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች በጋሞ ዞን ውስጥ በዩኒቨርሲቲው የሚደገፉ የጎልማሶች ትምህርት ማእከላት የትምህርት አሰጣጥና አፈጻጸማቸውን ከግንቦት 21-27/2015 ዓ/ም ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የጎልማሶች ትምህርትና ተግባር ተኮር አጫጭር ሥልጠናዎች በዳይሬክቶሬቱ በረዥም ጊዜ ፕሮግራም ከሚመሩ ሥራዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰው በዋናነት በዩኒቨርሲቲው ዙሪያና በአጎራባች አካባቢዎች ማንበብና መጻፍ የማይችል ትውልድ እንዳይኖርና ሳይማሩ የቆዩትን ወደ ትምህርት ዓለም እንዲቀላቀሉ ማድረግ ራእዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዳይሬክቶሬቱ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ባለሙያ አቶ አጥናፉ ባርባዱ በዳይሬክቶሬታቸው የሚመሩ በጋሞ ዞን ውስጥ 11 የጎልማሶች ትምህርት ማእከላት እንደሚገኙ ጠቁመው 2015 ዓ/ም የደረጃ አንድ እና ሁለት ተማሪዎች የትምህርት ቆይታ እንዲሁም በደረጃ ሁለት ትምህርታቸውን አጠናቀው ለምረቃ ብቁ የሆኑትን አፈጻጸም መገምገምና ከአመቻች መምህራን ጋር በውጤታቸው ዙሪያ ውይይት ማድረግ የጉዟቸው ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የሱልኣ ዛኮታ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት መምህር አቶ ኤርሚያስ አማረ በትምህርት ቤቱ ማስተማር ከጀመሩ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው ተናግረው ተማሪዎቹ በተሰጣቸው የተጠናከረ ትምህርት ማንበብና መጻፍ መቻላቸውንና ለትምህርቱ ፍቅር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው መምህር አቶ ኮከብ ወራሞ ተማሪዎች አብዛኛው አርሶ አደር በመሆናቸው ከሚሰጣቸው መደበኛ ትምህርት ጋር የዘር አዘራር፣ የእንሰትና ሌሎች ለምግብ የሚሆኑ ችግኞች እንዴት እንደሚተክሉና የመሳሰሉ ከተለመደው የአኗኗር ሁኔታቸው ጋር የተዛመዱ የግብርና ትምህርቶችን መማራቸው በጎ ተጽእኖ የሚያሳድርና በትምህርቱ ደስተኛ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የሱላ ዛኮላ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተማሪ የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ደማንቾ የጎልማሶች ትምህርት በአካባቢያቸው በመኖሩ መደሰታቸውን ገልጸው ከዚህ ቀደም ለመማር ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸውና የጎልማሶች ትምህርትን ከጀመሩ በኋላ መምህራን በሚሰጧቸው ትምህርት በመታገዝ ማንበብና መጻፍ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዓለማየሁ ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር ግብርናን አስመልክቶ መምህራን በሚሰጧቸው ተጨማሪ ዕውቀት በመታገዝ በትምህርት ቤቱ ሠርቶ ማሳያ በተግባር የፈተሿቸውንና የተሻሻሉ የግብርና ተሞክሮዎችን ወደ ራሳቸው የእርሻ መሬት በማውረድ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
የዳራማሎ ወረዳ ሆያ ዳጎዛ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተማሪ አቶ ኢሊጎ ኢራ ከትምህርቱ ባገኙት ዕውቀት መነሻነት ሌሎች በአካባቢያቸው የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትምህርት እንዲጀምሩና ያቋረጡትም ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ጥረት እንደሚያደርጉ እንዲሁም ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን የተማሩትን የጤና ትምህርት ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ አካባቢያቸው በማውረድ እየተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሼሌ፣ ዚጊቲ፣ ጫኖ ዶርጋና ላንቴ፣ በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የሱልኣ ዛኮላ፣ በዳራማሎ ወረዳ የሆያ ዳጎዛ፣ በምዕራብ አባያ ወረዳ ደልቦና አልጌ እንዲሁም በቁጫ ወረዳ ዲንኬን ጨምሮ ሌሎች በዩኒቨርሲቲው የሚደገፉ 11 የጎልማሶች ትምህርት የሚሰጥባቸው የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማእከላት ጉብኝት ተደርጎባቸዋል፡፡

በ2015 የትምህርት ዘመን በአጠቃላይ በማእከላቱ በደረጃ አንድ እና ሁለት 1,950 ጎልማሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሲገኙ 528ቱ ደረጃ ሁለትን አጠናቀው በሠኔ ወር መጨረሻ እንደሚመረቁ ተገልጿል፡፡ በቀጣይም ደረጃ ሁለትን ያጠናቀቁ ጎልማሶች በተሻሻለው መመሪያ መሠረት በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በቀጥታ ወደ 4ኛ ክፍል የሚሸጋገሩ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት