የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለአስተዳደር ዘርፍ አመራሮች ከግንቦት 21-25/2015 ዓ/ም በሕይወትና አእምሮ ውቅር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው የስኬታማ ሕይወት መርሆዎች፣ ማንነትንና የመኖርን ምክንያት ማወቅ፣ የግልና የተቋም ራእይ፣ ህልም እውን ማድረግና የመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ራስን ማወቅ ለግለሰብ፣ ለተቋም ብሎም ለሀገር እድገት አስፈላጊ በመሆኑ ለለውጥ ራስን ማዘጋጀት ይገባል ብለዋል፡፡ ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ከታች ላሉ ሠራተኞች ማሸጋገር እንዳለባቸው በማሳሰብ በሥራ ክፍሉ በቀጣይ ታቅደው የሚሠሩ መሰል ሥልጠናዎችን ስኬታማ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በበኩላቸው ሥልጠናው ለሁሉም ማኅበረሰብ ወሳኝና አስፈላጊ ሲሆን የጎደለንን ለማወቅና ያለንን በማሳደግ ራስን ለማነጽ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡

የፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቀልቦ የሰብእና ግንባታ ሥልጠናዎች ራስን ለማነጽና ለሀገር እድገት ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን አውስተው ሠልጣኞች ከሥልጠናው የሚያገኙትን ዕውቀት ካላቸው የትምህርት ዕውቀት ጋር በማጣመር ባሉበት የኃላፊነት ደረጃ የተሻለ አፈጻጸም ማምጣት እንዲችሉ የሚያግዝና አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተቋም ማንነት የሚለካው በሠራተኞቹ ውጤት ነው ያሉት የሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ የአመራሩን ቁመና በማስተካከል ለሚመሩት ሕዝብና ለሚያገለግሉት ተቋም ብቃት ያላቸው እንዲሆኑና ሕይወታቸውን በማደስ መልካም ሰብእናን ተላብሰው በታማኝነት ማገልገል እንዲችሉ ታልሞ ሥልጠናው የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በተሻለ መንገድ ሥልጠናው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊ የሆኑት አቶ መሰለ እሸቴ እና ወ/ሮ ዓለምነሽ ህዝቅኤል በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ማንነትን ፈትሾ ራስን በማግኘት በሚሠሩበት ተቋም ከመገልገል በዘለለ ጥሩ አገልጋይና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ለመሆን የሚረዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት