የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባሕልና ቋንቋ ተቋም ከማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ‹‹The Discovery of the First Fossil of Ethiopian Wolf (Canis Simensis)›› በሚል ርዕስ የጥናት ውጤትን ለሕዝብ ይፋ የማድረጊያ መርሃ-ግብር ግንቦት 28/2015 ዓ/ም አዘጋጅተዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ጥራት ያለው  ምርምርንና የመማር ማስተማር ተግባራትን በአንድነት አጋምዶ ማስቀጠል ዩኒቨርሲቲው በዓለም መድረክ ገጽታው ጎልቶ እንዲታይ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ መ/ፕሬዝደንቱ አክለውም ጥራት ያላቸው ምርምሮችን በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው በተማሩና በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ከፍተኛ ልምድ ካካበቱ ተመራማሪዎችና ምሁራን ጋር መሥራት ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በትብብር የሚሠሩ ምርምሮች ጥራት ላለው ምርምርና መማር ማስተማር ትልቅ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ በትኩረት እንደሚሠራም ተ/ፕ በኃይሉ ተናግረዋል፡፡  

ይህ ግኝት የከርሰ ምድር ጥናት መሆኑን የሚናገሩት ተ/ፕ በኃይሉ ቀይ ቀበሮዎች በቅርስ ረገድ ከኢትዮጵያ ውጪ የማይገኙና ውድ የሆኑ የዱር እንስሳት መሆናቸውን ገልጸው የዱር እንስሳቱ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ የሚሹ ናቸው ብለዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጠ የሚገኘው ሉላዊ የአየር ጸባይ ለውጥ ለእንስሳቱ ህልውና አሳሳቢ በመሆኑ እንስሳቱ ባሉበት አካባቢ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተ/ፕ በኃይሉ ጠቅሰዋል፡፡

ግኝቱ በዓለም ብቸኛ መሆኑን የጠቀሱት የዩኒቨርሲቲው የባሕልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ በበኩላቸው ግኝቱን ልዩ የሚያደርገው በኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ቡድን መሪነት የተገኘ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ አዲስ ነገር መፍጠርና መሥራት እንደምትችል ያስመሰከረ፣ ሀገሪቱ ለጀመረችው ልማት አዎንታዊ ሚና የሚጫወት እንዲሁም የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው የዱር እንስሳት ትኩረት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ግኝቱ እነዚህ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ትኩረት በማጣታቸው ምክንያት በቀጣይ ዓመታት ይበልጥ እንዳይጠፉ የመንግሥት አካላት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ አርሶና አርብቶ አደሮች እንስሳቱን በመጠበቅና በመንከባከብ ዙሪያ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ዶ/ር ሰኢድ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዋና ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በየትኛውም መስክ ምርምር የሚሠሩ ተመራማሪዎችን የሚያበረታታ ሲሆን በአርኪዮሎጂው ዘርፍ የተገኘውን አዲስ ግኝት ለማስቀጠል የዘርፉን ምርምር አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ በዘርፉም በትብብር በሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ሚና በአግባቡ እንደሚወጣ ጠቁመው በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከሂብሪው ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር የሚሠራበት መንገድ እንደሚመቻች ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹The Discovery of the First Fossil of Ethiopian Wolf, Implications for Evaluation and the Future Survival of the Species›› በሚል ርዕስ ተከናውኖ ለኅትመት የበቃውን የጥናት ውጤት ከዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ቡድን ጋር በመተባበር ያሳተሙት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና በኢየሩሳሌም ሂብሪው ዩኒቨርሲቲ አርኪዮሎጂ ኢንስቲትዩት /Hebrew University Archeology Institute/  ተመራማሪ ዶ/ር ተገኑ ጎሳ እንደገለጹት የ1.5 ሚሊየን ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ የታችኛው መንጋጋ ክፋይ እ.አ.አ በ2017 በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ በመልካ ዋከና መካነ ቅርስ ተገኝቷል፡፡ ቅሪት አካሉ የተገኘው ከባህር ጠለል በላይ በ2,300 ሜትር ከፍታ ላይ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ያሉ ቀይ ቀበሮዎች የሚኖሩት ከባህር ጠለል በላይ ከ3000 ሜትር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግኝቱ አሁን ካሉት የቀይ ቀበሮ ዝርያዎች ጋር ተመሳሳይ መሆንና አለመሆኑን፣ ግኝቱ ከሌሎች የቀበሮ ዝርያዎች ጋር ያለውን ግንኙነት የማረጋገጥና ዕድሜውን የመለካት፣ ከፍተኛ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ብርቅዬ ዝርያዎች ለመንከባከብና ለመታደግ ግኝቱ ያለውን አስተዋጽኦ፣ አሁን ያሉት የቀይ ቀበሮ ዝርያዎች እንዳይጠፉ የመጠበቁ ሥራ እንዲጠናከር ከማድረግ አንጻርና ውጤቱ ያለውን ፋይዳን ጨምሮ ለአምስት ዓመታት በተለያዩ ባለሙያዎች የማረጋገጥ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን እና ጥናቱ ለኅትመት እስከሚበቃበት ጊዜ ድረስም በብዙ የጥናት ሂደቶች ውስጥ ማለፉን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተገኑ ገለጻ የመካነ ቅርሱ ቅሪተ አካል እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ የቀይ ቀበሮ ዝርያ በኢትዮጵያ መኖር የጀመረበት ጊዜ በግልጽ የማይታወቅ ሲሆን ቀደም ብሎ በዓለም ላይ በሚገኙ የቀበሮ ዝርያዎች ዘረ-መል ላይ በተደረገ ጥናት የተገኘው ውጤትም የመጀመሪያው ቀይ ቀበሮ በኢትዮጵያ መኖር የጀመረው ጊዜ ከ100,000 ዓመት እንደማይበልጥና ጊዜውም ከፕሌይስቶሲን ዘመን መጨረሻ (Late Pleistocene Period) እንደማይዘል ያስቀመጠውን የምርምር ድምዳሜ ሙሉ በሙሉ የሚቀይርና ከቀዳሚው ምርምር ውጤት ግኝት ጊዜ  በአንድ መቶ ሺ ዕድሜ የረዘመ  ዕድሜ ያለው ቅሪተ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዱር እንስሳቱ ላይ የተጋረጡ ብዙ አሁናዊ ፈተናዎች አሉ ያሉት ተመራማሪው በዚህ ጥናት ሥና ምኅዳራዊ ሞዴሎች (Eco-Climatic Models) መረጃ መሠረት የቀይ ቀበሮ ዝርያዎች ከቤት ውሾች ወደ ቀበሮዎቹ በሚዛመት የእብድ ውሻ በሽታ በብዛት እየተጠቁ መሆናቸው፣ የቀይ ቀበሮ ዝርያዎቹ ብዛት ከ500 የማይበልጥና ከእነዚህም መካከል ለመራባት ብቁ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ከ200 በታች በመሆናቸው ምክንያት በአካባቢው ከሚገኙ ውሾች ጋር የመዳቀል ባህርይ ማምጣታቸው፣  የመኖሪያ አካባቢያቸው ከንኪኪ ነጻ አለመሆኑና ከሰውና ከሠፈራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመቀልበስ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን መሻገር ካልተቻለ እንስሳቱ የመጥፋት እድላቸው ሰፊ መሆኑን ዶ/ር ተገኑ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ተገኑ የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ቡድኑን በሂብሪው ዩኒቨርሲቲ መ/ር ከሆኑት ፕ/ር ኤርላ ሆቨርስ /Prof Erella Hovres/ ጋር መምራታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት