አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃና ልማት ጽ/ቤት፣  ጋሞ ዞን አስተዳዳር ጽ/ቤት፣ አርባ ምንጭ ከተማና ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳር ጋር በመተባባር ‹‹የፕላስቲክ ብክለት መፍትሔዎች/Solutions to Plastic Pollution›› በሚል መሪ ቃል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጋንታ ካንቻሜ ቀበሌ ጋንታ ተራራ ላይ 50ኛውን የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን ግንቦት 29/2015 ዓ/ም አክብሯል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የዛሬ 51 ዓመት በስዊዲን ስቶክሆልም ውስጥ አየር ንብረትን በሚመለከት የመጀመሪያው ስብሰባ መካሄዱን ተከትሎ በየዓመቱ የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን መከበር እንደተጀመረ ተናግረዋል፡፡ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ እና በሀገራችን ለ30ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ በዓሉን ማክበሩ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳዮችን ለሚከታተሉ ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቦች እንዲሁም ድጋፍና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሐሳባቸውን ለማራመድና የማኅበረሰብ ንቅናቄ ለመፍጠር ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ መልካሙ ቶንቼ አካባቢንና የተፈጥሮ ሀብትን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት የሁሉም ማኅበረሰብ ክፍል ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ መልካሙ በግብርናው ዘርፍ ምርታማ ለመሆን በተፋሰስ ሥራዎች አፈሩን ከጎርፍና ከመራቆት መከላከልና በአግባቡ ማልማት ያስፈልጋል፡፡ ጽ/ቤት ኃላፊው ‹‹ፕላስቲክ›› አፈር እንዳይለማ ከማድረጉ ባሻገር በጎርፍ አማካኝነት ወደ ሐይቆች በመግባት የሐይቆችን ብዝሃ ሕይወት የሚያዛባና የሚያጠፋ በመሆኑ ሁላችንም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አካባቢያችንን ከፕላስቲክ ብክለት መጠበቅ ይገባናል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አይካ በበኩለቸው በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ለአደጋ የተጋለጠውን ጫሞ ሐይቅና ሌሎች የአካባቢው ሀብቶችን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ቆም ብለን ማሰብ፣ መወያየትና መፍትሔ ማበጀት ይገባናል ብለዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ናዳና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በዞኑ ሲከሰቱ መቆየታቸውን ያስታወሱት ጽ/ቤት ኃላፊው የችግሩ መንስኤ የሆነውን የብዝሃ ሕይወት መመናመን ማሻሻልና የፕላስቲክ ውጤቶችን በአግባቡ በማስወገድ ብክለትን ማስቀረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም ሆነ በእለቱ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚገባም ጽ/ቤት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት የልማት ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ደፋሩ ደበበ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን ጋር በመተባባር በየዓመቱ የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀንን እንደሚያከብር አስታውሰው በዘንድሮው አከባበር የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በዞኑ የሚከሰተውን የመሬት መንሸራተትና ናዳ መጠን በቦታው ተገኝተው መመልከታቸውንና በቀጣይ የመፍትሔ አካል ለመሆንና የማኅበረሰብ ንቅናቄ ለመፍጠር 1,200 ችግኞችን በጋራ መትከላቸውን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት